መዝሙር 31:1-8
መዝሙር 31:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኀጢአታቸው የተተወላቸው፥ በደላቸውንም ሁሉ ያልቈጠረባቸው ብፁዓን ናቸው። እግዚአብሔር በደሉን የማይቈጥርበት በልቡም ሽንገላ የሌለበት ሰው ብፁዕ ነው። ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ብያለሁና አጥንቶቼ አረጁ፤ በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፥ እሾህ በወጋኝ ጊዜ ወደ ጕስቍልና ተመለስሁ። ኀጢአቴን ነገርሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ስለ ኀጢአቴ ወደ እግዚአብሔር ራሴን እከስሳለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ሽንገላ ተውልኝ። ስለዚህ ጻድቅ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይጸልያል፤ ነገር ግን ብዙ የጥፋት ውኃ ወደ አንተ አይቀርብም። አንተ ካገኘችኝ ከዚች መከራዬ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ከከበቡኝም ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ። አስተምርሃለሁ፥ በምትሄድባትም በዚች መንገድ አጸናሃለሁ። ዐይኖቼን በአንተ ላይ አጸናለሁ።
መዝሙር 31:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መጠጊያ አደረግሁ፤ ከቶም አልፈር፤ በጽድቅህም ታደገኝ። ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ፈጥነህ አድነኝ፤ መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤ ታድነኝም ዘንድ ምሽግ ሁነኝ። አንተ ዐለቴና መጠጊያዬ ነህና፣ ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤ መንገዱንም ጠቍመኝ። አንተ መጠጊያዬ ነህና፣ በስውር ከተዘረጋብኝ ወጥመድ አውጣኝ። መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ፤ እግዚአብሔር የእውነት አምላክ ሆይ፤ አንተ ተቤዠኝ። ለከንቱ ጣዖታት ስፍራ የሚሰጡትን ጠላሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ። በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ መከራዬን አይተሃልና፤ የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል። ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው።
መዝሙር 31:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! መጠጊያ እንድትሆነኝ ወደ አንተ መጥቻለሁ፤ ስለዚህ እንዳፍር አታድርገኝ፤ በጽድቅህም አድነኝ። ጌታ ሆይ! አድምጠኝ፤ ፈጥነህም በመምጣት አድነኝ፤ መጠጊያ አለትና ጠንካራ ምሽግ ሆነህ አድነኝ። አንተ መጠጊያ ምሽጌ ነህ፤ ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤ የምሄድበትንም መንገድ አሳየኝ። አንተ መጠጊያዬ ስለ ሆንክ ጠላቶቼ ከዘረጉብኝ ወጥመድ አውጣኝ። የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ነፍሴን ለአንተ እሰጣለሁና አድነኝ። ዋጋቢሶች ለሆኑ ጣዖቶች የሚሰግዱትን ሁሉ ትጠላለህ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ። ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ደስ ይለኛል፤ ሐሴትም አደርጋለሁ፤ መከራዬን አይተህ ጭንቀቴን ታውቃለህ፤ ለጠላቶች አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ሰፊ መንገድ ከፈትክልኝ።
መዝሙር 31:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ በአንተ ታመንሁ፥ ለዘለዓለም አልፈር፥ በጽድቅህም አድነኝ። ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፥ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ። አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም። አንተ መታመኛዬ ነህና ከደበቁብኝ ወጥመድ አውጣኝ። በእጅህ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ፥ የእውነት አምላክ አቤቱ፥ ተቤዥተኸኛል። ከንቱ ምናምንቴነትን የጠበቁትን ጠላህ፥ እኔ ግን በጌታ ታመንሁ። መከራዬን አይተሃልና፥ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና በምሕረትህ ደስ ይለኛል ሐሤትም አደርጋለሁ።