መዝሙር 30:8-12
መዝሙር 30:8-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ጠራሁህ፤ ምሕረትንም ለመንኩህ። እኔ ወደ መቃብር ብወርድ ምን ይጠቅምሃል? ወደ ዐፈርነት ከተለወጥሁ በኋላ እንዴት ላመሰግንህ እችላለሁ? ታማኝነትህንስ እንዴት መናገር ይቻለኛል? እግዚአብሔር ሆይ! ስማኝ፤ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ሆይ! እርዳኝ። አንተ ሐዘኔን ወደ ደስታ ለወጥክልኝ፤ ትካዜዬን ከእኔ አስወገድክልኝ፤ የማቅ ልብሴን አውልቀህ ደስታን አለበስከኝ። ስለዚህ ዝም አልልም፤ ለአንተ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ ስለዚህ ለዘለዓለም አመሰግንሃለሁ።
መዝሙር 30:8-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም፥ በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምህ። ተቸግሬአለሁና አቤቱ ይቅር በለኝ፥ ዐይኔም ከቍጣ የተነሣ ታወከች፥ ነፍሴም፥ ሆዴም። ሕይወቴ በመከራ አልቋልና፥ ዘመኔም በጩኸት፤ ኀይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ሁሉ ተነዋወጡ። በጠላቶቼ ሁሉ ዘንድ ተሰደብሁ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለዘመዶቼም አስፈሪ ሆንሁ፤ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ። እንደ ሞተ ሰው ከልብ ረሱኝ፥ እንደ ጠፋ ዕቃም ሆንሁ።
መዝሙር 30:8-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ ተጣራሁ፤ ወደ ጌታም እንዲህ ብዬ ጮኽሁ፤ “በእኔ ወደ ጕድጓድ መውረድ፣ በመሞቴ ምን ጥቅም ይገኛል? ዐፈር ያመሰግንሃልን? ታማኝነትህንስ ይናገራልን? እግዚአብሔር ሆይ፤ ስማ፤ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ረዳት ሁነኝ።” ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ፤ ማቄን አውልቀህ ፍሥሓን አለበስኸኝ፤ እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፤ ዝምም አትበል፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።