መዝሙር 30:1-7
መዝሙር 30:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘለዓለምም አልፈር፤ በጽድቅህም አስጥለኝ፥ አድነኝም። ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ አምላኬ መድኀኒቴና የመጠጊያዬ ቤት ሁነኝ። ኀይሌና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ ምራኝ፥ መግበኝም፤ አቤቱ፥ አንተ ረዳቴ ነህና ከሰወሩብኝ ከዚች ወጥመድ አውጣኝ። በእጅህ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ፤ የጽድቅ አምላክ እግዚአብሔር፥ ተቤዠኝ። ከንቱን ነገር የሚጠብቀውን ሁሉ ሁልጊዜ ጠላህ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ። በትድግናህ ደስ ይለኛል፤ ሐሴትም አደርጋለሁ። መከራዬን አይተሃልና፥ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና።
መዝሙር 30:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከታች አንሥተኸኛልና፣ ጠላቶቼም በላዬ እንዳይደሰቱ አድርገሃልና፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ትረዳኝ ዘንድ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ አንተም ፈወስኸኝ። እግዚአብሔር ሆይ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፤ ወደ ጕድጓድ ከመውረድም መልሰህ ሕያው አደረግኸኝ። እናንተ የምትታመኑት፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ቅዱስ ስሙንም አወድሱ። ቍጣው ለዐጭር ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል። እኔም በተረጋጋሁ ጊዜ፣ “ከቶ አልናወጥም” አልሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ሞገስ፣ ተራሮቼ ጸኑ፣ ፊትህን በሰወርህ ጊዜ ግን፣ ውስጤ ታወከ።
መዝሙር 30:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ስላዳንከኝና ጠላቶቼ በእኔ ላይ እንዲደሰቱ ስላላደረግህ እጅግ አመሰግንሃለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እንድትረዳኝ ወደ አንተ ተጣራሁ፤ አንተም ፈወስከኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፤ ወደ ጥልቁም ከመውረድ ሕይወቴን ጠበቅኸው። ለእርሱ ታማኞች አገልጋዮች የሆናችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን በዝማሬ አመስግኑት! ለቅዱስ ስሙም ምስጋና አቅርቡለት! እርሱ የሚቈጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን ለዘለዓለም ነው፤ ሌሊት ሲለቀስ ዐድሮ በማለዳ ደስታ ይሆናል። ዋስትና እንዳለኝ ስላወቅሁ “ከቶ አልሸነፍም” አልኩ። እግዚአብሔር ሆይ! ሞገስን በሰጠኸኝ ጊዜ እንደማይነቃንቅ ተራራ አበረታኸኝ፤ ፊትህን በሰወርክ ጊዜ ግን ተስፋ ቈረጥኩ።
መዝሙር 30:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ተቀብለኸኛልና፥ ጠላቶቼንም ደስ አላሰኘህብኝምና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ አንተም ፈወስከኝ። አቤቱ፥ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፥ ወደ ጉድጓድም እንዳልወርድ አዳንኸኝ። ቅዱሳን ሆይ፥ ለጌታ ዘምሩ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ። ቁጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፥ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል። እኔም በደስታዬ፦ ለዘለዓለም አልታወክም አልሁ።