መዝሙር 30:1-5
መዝሙር 30:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘለዓለምም አልፈር፤ በጽድቅህም አስጥለኝ፥ አድነኝም። ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ አምላኬ መድኀኒቴና የመጠጊያዬ ቤት ሁነኝ። ኀይሌና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ ምራኝ፥ መግበኝም፤ አቤቱ፥ አንተ ረዳቴ ነህና ከሰወሩብኝ ከዚች ወጥመድ አውጣኝ። በእጅህ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ፤ የጽድቅ አምላክ እግዚአብሔር፥ ተቤዠኝ።
መዝሙር 30:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከታች አንሥተኸኛልና፣ ጠላቶቼም በላዬ እንዳይደሰቱ አድርገሃልና፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ትረዳኝ ዘንድ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ አንተም ፈወስኸኝ። እግዚአብሔር ሆይ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፤ ወደ ጕድጓድ ከመውረድም መልሰህ ሕያው አደረግኸኝ። እናንተ ቅዱሳኑ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ቅዱስ ስሙንም አወድሱ። ቍጣው ለዐጭር ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል።
መዝሙር 30:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ስላዳንከኝና ጠላቶቼ በእኔ ላይ እንዲደሰቱ ስላላደረግህ እጅግ አመሰግንሃለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እንድትረዳኝ ወደ አንተ ተጣራሁ፤ አንተም ፈወስከኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፤ ወደ ጥልቁም ከመውረድ ሕይወቴን ጠበቅኸው። ለእርሱ ታማኞች አገልጋዮች የሆናችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን በዝማሬ አመስግኑት! ለቅዱስ ስሙም ምስጋና አቅርቡለት! እርሱ የሚቈጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን ለዘለዓለም ነው፤ ሌሊት ሲለቀስ ዐድሮ በማለዳ ደስታ ይሆናል።