መዝሙር 21:1-7
መዝሙር 21:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አምላኬ፥ አምላኬ፥ ተመልከተኝ፥ ለምን ተውኸኝ? የኀጢአቴ ቃል እኔን ከማዳን የራቀ ነው። አምላኬ፥ በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አልሰማኸኝም። በሌሊትም በፊትህ አላሰብከኝም። በእስራኤል የተመሰገንህ አንተ ግን በቅዱሳንህ ትኖራለህ። አባቶቻችን አንተን አመኑ፥ አመኑ፥ አንተም አዳንሃቸው። ወደ አንተ ጮኹ፥ ዳኑም፥ አንተንም አመኑ፥ አላፈሩም። እኔ ግን ትል ነኝ፥ ሰውም አይደለሁም፤ በሰው ዘንድ የተናቅሁ፥ በሕዝብም ዘንድ የተዋረድሁ ነኝ። የሚያዩኝ ሁሉ ይጠቃቀሱብኛል፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይላሉ፦
መዝሙር 21:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ንጉሥ በኀይልህ ደስ ይለዋል፤ በምትሰጠውም ድል እጅግ ሐሤት ያደርጋል። የልቡን መሻት ሰጠኸው፤ የከንፈሮቹንም ልመና አልከለከልኸውም። ሴላ መልካም በረከት ይዘህ በመንገዱ ላይ ጠብቀኸው፤ የንጹሕ ወርቅ ዘውድም በራሱ ላይ ደፋህለት። ሕይወትን ለመነህ፤ ረዥም ዘመናትንም እስከ ዘላለም ሰጠኸው። በአቀዳጀኸው ድል ክብሩ ታላቅ ሆነ፤ ክብርንና ግርማን አጐናጸፍኸው። ዘላለማዊ በረከትን ሰጠኸው፤ ከአንተ ዘንድ በሚገኝ ፍሥሓም ደስ አሠኘኸው፤ ንጉሡ በእግዚአብሔር ተማምኗልና፤ ከልዑልም ጽኑ ፍቅር የተነሣ፣ ከቆመበት አይናወጥም።
መዝሙር 21:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ኀይልን ስለ ሰጠኸው ንጉሥ ደስ ብሎታል፤ ድልን ስለ አቀዳጀኸውም ሐሴት ያደርጋል። የልቡን ምኞት ሰጥተኸዋል፤ የለመነህንም አልከለከልከውም። በብዙ በረከትን ሰጥተህ ተቀበልከው፤ በራሱ ላይ የንጹሕ ወርቅ ዘውድ ደፋህለት። ሕይወትን እንድትሰጠው ለመነህ፤ አንተም ረጅም ዕድሜና ዘለዓለማዊ የሆነ ሕይወትን ሰጠኸው። አንተ በሰጠኸው ድሎች ምክንያት ታላቅ ክብር አገኘ፤ ክብርንና ግርማን አቀዳጀኸው። የዘለዓለም በረከትን ሰጠኸው፤ አንተም ከእርሱ ጋር በመገኘትህ ደስ ታሰኘዋለህ፤ ንጉሡ የሚተማመነው በእግዚአብሔር ነው፤ የማያቋርጠው የልዑል እግዚአብሔር ፍቅር ከእርሱ ጋር ስለ ሆነም አይናወጥም።
መዝሙር 21:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፥ በማዳንህም እንዴት አብዝቶ ሐሤትን ያደርጋል! የልቡን ፈቃድ ሰጠኽው፥ የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም። በበጎ በረከት ደርሰህለታልና፥ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ። ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም፥ ለረጅም ዘመን ለዘለዓለም ዓለም። በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፥ ሞገስንና ግርማን በላዩ አኖርህ። የዘለዓለም በረከትን ሰጥተኸዋልና፥ በፊትህም ደስ ታሰኘዋለህ።