መዝሙር 147:1-11
መዝሙር 147:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሃሌ ሉያ። አምላካችንን በመዝሙር ማወደስ እንዴት መልካም ነው! እርሱን ማመስገን ደስ ያሰኛል፤ ይህ ተገቢም ነው። እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን መልሶ ይሠራታል፤ ከእስራኤል የተበተኑትን ይሰበስባል። ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል። የከዋክብትን ብዛት ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል። ጌታችን ታላቅ ነው፤ እጅግ ኀያልም ነው፤ ለጥበቡም ወሰን የለውም። እግዚአብሔር ትሑታንን ከፍ ያደርጋል፤ ክፉዎችን ግን ወደ ምድር ይጥላል። ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ፤ ለአምላካችንም በመሰንቆ ምስጋና አቅርቡ። ሰማይን በደመናት የሚሸፍን እርሱ ነው፤ ለምድርም ዝናብን ይሰጣል፤ በተራሮችም ላይ ሣር ያበቅላል። ለእንስሳት ምግባቸውን፣ የቍራ ጫጩቶችም ሲንጫጩ የሚበሉትን ይሰጣቸዋል። እርሱ በፈረስ ኀይል አይደሰትም፤ በሯጭም ብርታት ላይ ደስታውን አያደርግም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል።
መዝሙር 147:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርን አመስግኑ! ለአምላካችን የምስጋና መዝሙር ማቅረብ መልካም ነው፤ እርሱን ማመስገን ደስ የሚያሰኝና ተገቢ ነው። እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድሳል፤ ከእስራኤል የተሰደዱትንም ይመልሳል። ልባቸው የተሰበረባቸውን ይፈውሳል፤ ቊስላቸውንም ይጠግናል። የከዋክብትን ብዛት ቈጥሮ ያውቃል፤ እያንዳንዳቸውንም በየስማቸው ይጠራቸዋል። አምላካችን ታላቅና ኀያል ነው፤ ለዕውቀቱም ወሰን የለውም። ትሑታንን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ክፉ አድራጊዎችን ግን በምድር ላይ ጥሎ ያዋርዳቸዋል። ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤ በገና እየደረደራችሁ ለአምላካችን ዘምሩ። እርሱ ደመናን በሰማይ ላይ ይዘረጋል፤ ለምድር ዝናብን ይሰጣል፤ ተራራዎችንም በለምለም ሣር ይሸፍናል። ለእንስሶች ምግብን ይሰጣል፤ ምግብ አጥተው የሚጮኹ የቊራ ጫጩቶችንም ይመግባል። የእርሱ ደስታ በብርቱ ፈረሶችና፤ በጦረኞች ኀይል አይደለም። እርሱን ደስ የሚያሰኙት በአክብሮት የሚፈሩትና በዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሚታመኑ ሰዎች ናቸው።
መዝሙር 147:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው። ጌታ ኢየሩሳሌምን ይሠራል፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ይሰበስባል። ልባቸው የተሰበረባቸውን ይፈውሳል፥ ሕማማቸውንም ይጠግናል። የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል። ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር ስፍር የለውም። ጌታ የተዋረዱትን ያነሣል፥ ክፉዎችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል። ለጌታ በምስጋና ዘምሩ፥ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ፥ ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፥ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል። ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል ለሚጠሩት ለቁራዎች ጫጩቶችም እንዲሁ። በፈረስ ኃይል አይደሰትም፥ በሰውም ጡንቻ ሐሴት አያደርግም። ጌታ በሚፈሩት፥ በጽኑ ፍቅሩ በሚታመኑት ይደሰታል።