መዝሙር 145:1-12

መዝሙር 145:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አምላኬና ንጉሤ ሆይ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህን ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ። በየቀኑ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ ታላቅነቱም አይመረመርም። ሥራህን አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ ያስተጋባል፤ ብርቱ ሥራህን ያውጃል። ስለ ግርማህ ውበትና ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ድንቅ ሥራህም ያወራሉ። ስለ ድንቅ ሥራህ ብርታት ይነጋገራሉ፤ እኔም ስለ ታላቅነትህ ዐውጃለሁ። የበጎነትህን ብዛት በደስታ ያወሳሉ፤ ስለ ጽድቅህም በእልልታ ይዘምራሉ። እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ታማኝነቱም የበዛ ነው። እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግንሃል፤ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል። ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤ በዚህም ለሰው ልጆች ብርቱ ሥራህን፣ የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ።

መዝሙር 145:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አምላኬና ንጉሤ ሆይ! ታላቅነትህን ዐውጃለሁ፤ ለዘለዓለምም አመሰግንሃለሁ። በየቀኑ አመሰግንሃለሁ፤ ለዘለዓለምም ስምህን አከብራለሁ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ከፍተኛ ምስጋናም የሚገባው ነው፤ ታላቅነቱም ሰው ከሚያስተውለው በላይ ነው። አንድ ትውልድ የአንተን ሥራ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላልፋል፤ ድንቅ ሥራህንም ይገልጣል። ሕዝቦች ስለ ክብርህና ስለ ግርማህ ታላቅነት ያወራሉ፤ እኔም ድንቅ ስለ ሆነው ሥራህ አሰላስላለሁ። ሕዝቦች አስደናቂ ስለ ሆኑት ታላላቅ ሥራዎችህ ይናገራሉ፤ እኔም ታላቅነትህን ዐውጃለሁ። ስለ ደግነትህ ገናናነት ይናገራሉ፤ ስለ ጽድቅህ ኀይል ከፍ ባለ ድምፅ ይዘምራሉ። እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው፤ ለቊጣ የዘገየና በዘለዓለማዊ ፍቅር የተሞላ ነው። እርሱ ለሰው ሁሉ ቸር ነው፤ ለፍጡሮቹም ሁሉ ይራራል። እግዚአብሔር ሆይ! ፍጡሮችህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ ሕዝቦችህም ሁሉ ያወድሱሃል። ስለ ንጉሥነትህ ክብር ያወራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይናገራሉ። በዚህ ዐይነት ሰዎች ሁሉ በኀይልህ ስላደረግሃቸው ታላላቅ ሥራዎችና ስለ መንግሥትህም ታላቅ ግርማ ያውቃሉ።