መዝሙር 143:7-12
መዝሙር 143:7-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እጅህን ከአርያም ላክ፥ ከብዙ ውኃም አድነኝ፤ ከባዕድ ልጆችም እጅ፥ አፋቸው ከንቱ ነገርን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የዐመፃ ቀኝ ከሆነ አስጥለኝ። አቤቱ፥ በአዲስ ምስጋና አመሰግንሃለሁ፤ ዐሥር አውታር ባለው በገናም እዘምርልሃለሁ። ለነገሥታት መድኀኒትን የሚሰጥ፥ ባሪያው ዳዊትን ከክፉ ጦር የሚያድነው እርሱ ነው። አፋቸውም ከንቱ ነገርን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የዐመፃ ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አድነኝ፥ አስጥለኝም። ልጆቻቸው በጐልማስነታቸው እንደ አዲስ ተክል የሆኑ፥ ሴቶች ልጆቻቸውም እንደ እልፍኝ ያማሩና ያጌጡ፤
መዝሙር 143:7-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈጥነህ መልስልኝ፤ መንፈሴ ደከመች፤ ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልሆን፣ ፊትህን ከእኔ አትሰውር። በአንተ ታምኛለሁና፣ በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና፣ የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መሰወሪያ አድርጌአለሁና፣ ከጠላቶቼ አድነኝ። አንተ አምላኬ ነህና፣ ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ፤ መልካሙ መንፈስህም፣ በቀናችው መንገድ ይምራኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራ አውጣት። ጠላቶቼንም ለእኔ ስላለህ ምሕረት ደምስሳቸው፤ እኔ ባሪያህ ነኝና፣ ነፍሴን የሚያስጨንቋትን ሁሉ አጥፋቸው።
መዝሙር 143:7-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! መንፈሴ ስለ ዛለብኝ ፈጥነህ መልስ ስጠኝ! ፊትህን ከእኔ አትሰውርብኝ! አለበለዚያ ወደ ጥልቁ ጒድጓድ እንደሚወርዱት ሰዎች እሆናለሁ። የምተማመነው በአንተ ስለ ሆነ በየጠዋቱ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ ሕይወቴን በዐደራ ለአንተ ስለ ሰጠሁ የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ስለ ተማጠንኩ ከጠላቶቼ አድነኝ። አንተ አምላኬ ነህ፤ ፈቃድህን እንዳደርግ አስተምረኝ፤ በመልካም ቸርነትህ በደኅና መንገድ ምራኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ክብርህ ሕይወቴን ጠብቅ፤ በእውነተኛነትህም ከችግሬ ሁሉ ነጻ አውጣኝ። ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥልኝ፤ ጠላቶቼን አጥፋቸው፤ እኔ አገልጋይህ ስለ ሆንኩ ጥቃት የሚያደርሱብኝን ሁሉ ደምስሳቸው።
መዝሙር 143:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፥ መንፈሴ ዛለ፥ ፊትህን ከኔ አትሰውር፥ ወደ ጉድጓድም እንደሚወርዱ እንዳልሆን። አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ጽኑ ፍቅርህን አሰማኝ፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አሳውቀኝ። አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ። አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፥ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ። አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፥ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት። በጽኑ ፍቅርህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባርያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው።