መዝሙር 141:1-5
መዝሙር 141:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ለመንሁ። ልመናዬን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ መከራዬንም በፊቱ እናገራለሁ። ሰውነቴ በላዬ ላይ ባለቀች ጊዜ አቤቱ፥ መንገዴን አንተ ታውቃለህ፤ በምሄድባት በዚያች መንገድ ወጥመድን ሰወሩብኝ። ወደ ቀኝም ተመልሼ አየሁ፥ የሚያውቀኝም አጣሁ፤ መሸሸጊያም የለኝም፥ ስለ ሰውነቴም የሚመራመር የለም። አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፦ “አንተ ተስፋዬ ነህ፥ በሕያዋንም ምድር አንተ ዕድል ፋንታዬ ነህ” አልሁ።
መዝሙር 141:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ፤ ወደ አንተ ስጣራም ድምፄን ስማ። ጸሎቴ በፊትህ እንደ ዕጣን ትቈጠርልኝ፤ እጄን ማንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን። እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአፌ ጠባቂ አድርግ፤ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ። ከዐመፀኞች ጋር፣ በክፉ ሥራ እንዳልተባበር፣ ልቤን ወደ ክፉ አታዘንብል፤ ከድግሳቸውም አልቋደስ። ጻድቅ ሰው ይቅጣኝ፤ ይህ በጎነት ነው፤ ይገሥጸኝም፤ በራሴ ላይ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፤ ራሴም ይህን እንቢ አይልም። ጸሎቴ ግን በክፉዎች ተግባር ላይ ነው፤
መዝሙር 141:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ወደ አንተ እጣራለሁ፤ በፍጥነትም እርዳኝ! ወደ አንተም ስጮኽ ስማኝ! ጸሎቴን እንደ ዕጣን፥ የተዘረጉትን እጆቼን እንደ ማታ መሥዋዕት አድርገህ ተቀበል። እግዚአብሔር ሆይ! ለአፌ ጠባቂ አኑር፤ በከንፈሮቼም በር ላይ ዘበኛ አቁም። ስሕተት ለማድረግ ከመመኘትና ከክፉ አድራጊዎች ጋር በክፉ ሥራ ከመተባበር ጠብቀኝ፤ የበዓላቸው ግብዣ ተካፋይ ከመሆን ጠብቀኝ። ደግ ሰው በቅንነት መንፈስ ሊቀጣኝና ሊገሥጸኝ ይችላል፤ ከክፉ ሰዎች ግን ክብርን እንኳ አልቀበልም፤ ዘወትርም ክፉ ሥራቸውን በመቃወም እጸልያለሁ።
መዝሙር 141:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ በፍጥነት ድረስልኝ፥ ወደ አንተ ስጮኽም የልመናዬን ድምፅ ስማ። ጸሎቴ በፊትህ እንደ ዕጣን፥ እጆቼን ማንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ይሁን። አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ። ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፅን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለክፋት ምክንያት እንዳልሰጥ፥ ከድግሳቸውም አልቅመስ። ጻድቅ በጽኑ ፍቅር ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የክፉ ሰው ዘይት ግን ራሴን አይቀባ፥ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና።