መዝሙር 139:7-18
መዝሙር 139:7-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤ መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ። በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበርር፣ እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣ በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች። እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣ ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤ ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና። አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤ በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ። አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው! ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር። ተኛሁም ነቃሁም፣ ገና ከአንተው ጋር ነኝ።
መዝሙር 139:7-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከአንተ ለማምለጥ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ከፊትህስ ርቄ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ እዚያ ትገኛለህ፤ ወደ ሙታን ዓለም ብወርድ በዚያም አንተ አለህ። ከፀሐይ መውጫ ባሻገር በርሬ ብሄድ፥ ወይም በፀሐይ መግቢያ በኩል ርቄ ብኖር፥ እዚያ ተገኝተህ በእጅህ ትመራኛለህ፤ በቀኝ እጅህም ትደግፈኛለህ። ጨለማን “ሰውረኝ” ወይም ብርሃንን “ወደ ሌሊት ተለወጥልኝ” ብል ጨለማ እንኳ በአንተ ዘንድ አይጨልምም፤ ሌሊቱም የቀን ያኽል ያበራል፤ ስለዚህ በአንተ ዘንድ ጨለማና ብርሃን ልዩነት የላቸውም። ሁለንተናዬን የፈጠርክ አንተ ነህ፤ በእናቴ ማሕፀን አገጣጥመህ የሠራኸኝ አንተ ነህ። በሚያስፈራና በሚያስገርም ሁኔታ ስለ ተፈጠርኩ አመሰግንሃለሁ፤ ሥራዎችህ ሁሉ አስደናቂዎች መሆናቸውን ጠንቅቄም ዐውቃለሁ። በድብቁ ቦታ በተሠራሁ ጊዜና በጥልቁ መሬት ውስጥ በአንድነት በተገጣጠምኩ ጊዜ ሰውነቴ ለአንተ ድብቅ አልነበረም። ከመወለዴ በፊት አየኸኝ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝ ቀኖቼ ገና ከመጀመራቸው በፊት በመዝገብህ ሰፍረዋል። አምላክ ሆይ! ሐሳብህ እጅግ የከበረና የሰፋ ስለ ሆነ እኔ ልረዳው አልችልም። ሐሳብህ ቢቈጠር ከባሕር አሸዋ የበዛ ነው፤ ቈጥሬ ልጨርስ ብፈልግ ዘለዓለማዊ መሆን ይኖርብኛል።
መዝሙር 139:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ቢሆን፥ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፥ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። አቤቱ፥ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፥ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዐይኖችህ አዩ፥ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። አቤቱ፥ ሐሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቁጥራቸውም እንደምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፥ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ።