መዝሙር 139:19-24
መዝሙር 139:19-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ሆይ፤ ክፉዎችን ብትገድላቸው ምናለበት! ደም የተጠማችሁ ሰዎች ሆይ፤ ከእኔ ራቁ! ስለ አንተ በክፋት ይናገራሉና፤ ጠላቶችህም ስምህን በከንቱ ያነሣሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚጠሉህን አልጠላምን? በአንተ ላይ የሚነሡትንስ አልጸየፍምን? በፍጹም ጥላቻ ጠልቻቸዋለሁ፤ ባላጋራዎቼም ሆነዋል። እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።
መዝሙር 139:19-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ምነው ክፉዎችን ባጠፋህ! ምነው የደም ሰዎችንም ከእኔ ባራቅህ! እነርሱ በአንተ ላይ ክፉ ነገር ይናገራሉ፤ በጠላትነትም ስምህን በክፉ ያነሣሉ። እግዚአብሔር ሆይ! የሚጠሉህን እጅግ እጠላቸዋለሁ! በአንተ ላይ የሚያምፁትንም እጅግ እጸየፋቸዋለሁ! በብርቱ እጠላቸዋለሁ፤ እንደ ጠላቶቼም እቈጥራቸዋለሁ። አምላክ ሆይ! መርምረኝ፤ ልቡናዬንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ። በእኔ ውስጥ በደል እንዳለ ተመልከት፤ በዘለዓለማዊውም መንገድ ምራኝ።
መዝሙር 139:19-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ አንተ ክፉዉን የምትገድል ከሆንህስ፥ የደም ሰዎች ሆይ፥ “ከእኔ ፈቀቅ በሉ”። በክፋት ይናገሩብሃልና፥ ጠላቶችህም በከንቱ ያምፁብሃል። አቤቱ፥ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? በአንተ ላይ የሚነሡትንም አልናቅሁምን? ጨርሶ ጠላኋቸው፥ ጠላቶችም ሆኑኝ። አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፥ ፈትነኝ መንገዴንም እወቅ፥ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፥ የዘለዓለምንም መንገድ ምራኝ።