መዝሙር 139:1-6
መዝሙር 139:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ ከዐመፀኛ ሰውም ታደገኝ፥ ሁልጊዜ በልባቸው ዐመፃን የሚመክሩ፥ ይገድሉኝ ዘንድ ይከብቡኛል። ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ። አቤቱ፥ ከኃጥኣን እጅ ጠብቀኝ፥ እርምጃዬንም ሊያሰናክሉ ከመከሩ ከዐመፀኞች ሰዎች አድነኝ። ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፤ በመንገዴም ዕንቅፋትን አኖሩ። እግዚአብሔርንም፥ “አንተ አምላኬ ነህ፤ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ” አልሁት።
መዝሙር 139:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ። መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤ መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣ እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ። አንተ ከኋላም ከፊትም ዙሪያዬን ከለልኸኝ፤ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እንዲህ ያለው ዕውቀት ለእኔ ድንቅ ነው፤ ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው።
መዝሙር 139:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! መርምረህ ዐውቀኸኛል። አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሣ ታውቃለህ፤ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ ሆነህ ታስተውላለህ። የምጓዝበትንና የማርፍበትን ቦታ ታስተውላለህ፤ ተግባሬን ሁሉ ታውቃለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ገና ከመናገሬ በፊት ምን ለማለት እንደማስብ ታውቃለህ። በዙሪያዬ ሁሉ ትገኛለህ፤ በኀይልህም ትጠብቀኛለህ። የአንተ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ ነው፤ እኔ ላስተውለው ከምችለው በላይ ነው።