መዝሙር 119:9-20
መዝሙር 119:9-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣ በከንፈሬ እናገራለሁ። ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል። ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ። በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልዘነጋም። ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ ለአገልጋይህ መልካም አድርግ። ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት። እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር። ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ ነፍሴ እጅግ ዛለች።
መዝሙር 119:9-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወጣቶች ሕይወታቸውን በንጽሕና መጠበቅ የሚችሉት ትእዛዞችህን በመፈጸም ነው። አንተን በሙሉ ልቤ ስለምፈልግህ ትእዛዞችህን እንዳላፈርስ ጠብቀኝ። አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ የአንተን ሕግ አስተምረኝ። አንተ የሰጠኸውን ሕግ ሁሉ መላልሼ አነባለሁ። የአንተን ትእዛዝ መፈጸም ብዙ ሀብት የማግኘትን ያኽል ያስደስተኛል። ሥርዓትህን አጠናለሁ፤ በምትመራኝ መንገድ ላይም አተኲራለሁ። በሕግህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። በሕይወት እንድኖርና የቃልህን ትምህርት እንድጠብቅ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ። በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት ማየት እንድችል ዐይኖቼን ክፈትልኝ። እኔ በምድር ላይ በእንግድነት የምኖረው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ትእዛዞችህን አትሰውርብኝ። ነፍሴ ሥርዓትህን ለማግኘት ሁልጊዜ በመናፈቅ ተጨነቀች።
መዝሙር 119:9-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው። በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ። ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ። በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም። ለአገስልጋይህ መልካም አድርግለት፤ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ። ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ። እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። ፍርዶችህን ሁልጊዜ በመፈለግ ነፍሴ በናፍቆት ደቀቀች።