መዝሙር 119:6-16
መዝሙር 119:6-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያን ጊዜ አላፍርም። የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣ በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ ፈጽመህ አትተወኝ። ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣ በከንፈሬ እናገራለሁ። ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል። ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ። በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልዘነጋም።
መዝሙር 119:6-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ከአስተዋልኩ ኀፍረት ከቶ አይደርስብኝም። የሕግህን ፍጹምነት ባወቅሁ መጠን በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ስለምፈጽም ፈጽሞ አትተወኝ። ወጣቶች ሕይወታቸውን በንጽሕና መጠበቅ የሚችሉት ትእዛዞችህን በመፈጸም ነው። አንተን በሙሉ ልቤ ስለምፈልግህ ትእዛዞችህን እንዳላፈርስ ጠብቀኝ። አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ የአንተን ሕግ አስተምረኝ። አንተ የሰጠኸውን ሕግ ሁሉ መላልሼ አነባለሁ። የአንተን ትእዛዝ መፈጸም ብዙ ሀብት የማግኘትን ያኽል ያስደስተኛል። ሥርዓትህን አጠናለሁ፤ በምትመራኝ መንገድ ላይም አተኲራለሁ። በሕግህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም።
መዝሙር 119:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና። አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ። ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው። በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ። ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ። በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም።