የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 119:49-72

መዝሙር 119:49-72 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤ በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና። ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት። እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤ እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ። ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ ቍጣ ወረረኝ። በእንግድነቴ አገር፣ ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ ሕግህንም እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ ይህችም ተግባሬ ሆነች። እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ። በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤ እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ። መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም። የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም። ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣ በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል። በትእዛዞችህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ። እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤ አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ። አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤ እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤ እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ። ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣ በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።

መዝሙር 119:49-72 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ተስፋ የማደርገው በእርሱ ላይ ስለ ሆነ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አስብ። የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፥ በመከራዬ ጊዜ እንኳ እጽናናለሁ። ትዕቢተኞች ዘወትር ያፌዙብኛል፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ አልርቅም። እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለ ሆነ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ። ክፉ ሰዎች ሕግህን ሲተላለፉ በማየቴ በብርቱ ተቈጣሁ። በምኖርበት ቦታ ሁሉ ሕጎችህ የመዝሙሬ አዝማቾች ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! በሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ፤ በሕግህም ጸንቼ እኖራለሁ። ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥ በረከትን አገኘሁ። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤ ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ። በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ ከልብ እለምንሃለሁ። አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ። ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ። ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም እኔ ግን ሕግህን አልረሳም። ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ። አንተን የሚፈሩትንና ሕግህን የሚያከብሩትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ምድር በዘለዓለማዊው ፍቅርህ የተሞላች ናት፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የተስፋ ቃልህን ጠብቀሃል፤ ለእኔም ለአገልጋይህ ቸር ሆነሃል። በትእዛዞችህ ስለምተማመን አስተዋይነትንና ዕውቀትን ስጠኝ። አንተ እኔን ከመቅጣትህ በፊት እሳሳት ነበር፤ አሁን ግን ለቃልህ እታዘዛለሁ። አንተ ቸር ስለ ሆንክ ቸር የሆነውን ታደርጋለህ፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። ምንም እንኳ ትዕቢተኞች በሐሰት ስሜን ቢያጠፉ እኔ ትእዛዞችህን በሙሉ ልቤ እጠብቃለሁ። እነርሱ ትዕቢተኞችና ስሜተ ቢሶች ናቸው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሕግህን እንድማር ስላደረገኝ መቀጣቴ መልካም ሆነልኝ። ከብዙ ወርቅና ከብዙ ብር ይልቅ ለእኔ እጅግ ዋጋ ያለው አንተ የምትሰጠው ሕግ ነው።

መዝሙር 119:49-72 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ለባርያህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃልህን አስብ። ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ። ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፥ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም። ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም። ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኀዘን ያዘኝ። በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ። አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ። ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ። ጌታ ድርሻዬ ነው፥ ቃልህን እጠብቃለሁ አልሁ። በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፥ እንደ ቃልህ ማረኝ። ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፥ ሥርዓትህን አስተምረኝ። አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባርያህ መልካም አደረግህ። በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ። በፊት ስቼ ከመንገድህ ርቄ ነበር፥ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ። የትዕቢተኞች ዓመጽ በላዬ በዛ፥ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ። ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፥ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ዮድ።