መዝሙር 119:18-27
መዝሙር 119:18-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት። እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር። ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ ነፍሴ እጅግ ዛለች። ከትእዛዞችህ የሳቱትን፣ እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ። ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣ ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ። ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣ አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል። ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤ መካሪዬም ነው። ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።
መዝሙር 119:18-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት ማየት እንድችል ዐይኖቼን ክፈትልኝ። እኔ በምድር ላይ በእንግድነት የምኖረው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ትእዛዞችህን አትሰውርብኝ። ነፍሴ ሥርዓትህን ለማግኘት ሁልጊዜ በመናፈቅ ተጨነቀች። የተረገሙትንና ከትእዛዞችህ የሚያፈነግጡትን ትዕቢተኞች ትገሥጻለህ። እኔ ሕግህን ስለ ጠበቅሁ ስድባቸውንና ንቀታቸውን ከእኔ አርቅልኝ። መሪዎች ተሰብስበው በእኔ ላይ ቢዶልቱም እንኳ እኔ አገልጋይህ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። ትእዛዞችህ ያስደስቱኛል፤ መካሪዎቼም እነርሱ ናቸው። ተሸንፌ ትቢያ ላይ ወድቄአለሁ፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። አድራጎቴን ሁሉ ተናዘዝኩ፤ አንተም ሰማኸኝ፤ እንግዲህ ሕግህን አስተምረኝ። ሕግህን እንዳስተውል እርዳኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።
መዝሙር 119:18-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ። እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። ፍርዶችህን ሁልጊዜ በመፈለግ ነፍሴ በናፍቆት ደቀቀች። ከትእዛዛትህ የሚያፈነግጡተን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ገሠጽህ። ሕግህን ጠብቄአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ። መስፍኖች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፥ አገልጋይህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር። ሕግህም ተድላዬ ነው፥ ደንቦችህም አማካሪዎቼ ናቸው። ነፍሴ ወደ አፈር ተጠጋች፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መንገዶቼን ዘረዘርሁ፥ ሰማኸኝም፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። የድንጋጌዎችህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ።