መዝሙር 119:169-176
መዝሙር 119:169-176 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ታደገኝ። ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ። ትእዛዞችህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣ አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር። ትእዛዝህን መርጫለሁና፣ እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ደስታዬ ነው። አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ ሕግህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዞችህን አልረሳሁምና፣ ባሪያህን ፈልገው።
መዝሙር 119:169-176 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን ለማግኘት ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። ሕግህን ስለምታስተምረኝ ዘወትር አመሰግንሃለሁ። ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክለኞች ስለ ሆኑ፥ ስለ ቃልህ እዘምራለሁ። ትእዛዞችህን ስለ መረጥኩ፥ እኔን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ሁን። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን እናፍቃለሁ፤ በሕግህም ደስ ይለኛል። አንተን ለማመስገን እንድችል ዕድሜዬን አርዝምልኝ፤ ሥርዓትህም ረዳቴ ይሁን። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዤአለሁ፤ ነገር ግን ትእዛዞችህን ስላልረሳሁ፥ እኔን አገልጋይህን ፈልገኝ።
መዝሙር 119:169-176 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፥ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ። ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፥ እንደ ቃልህ አድነኝ። ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ። ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ። ትእዛዛትህን መርጫለሁና እጅህ የሚያድነኝ ይሁን። አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፥ ሕግህም ተድላዬ ነው። ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንህማለች፥ ፍርድህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፥ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባርያህን ፈልገው።