መዝሙር 119:137-160

መዝሙር 119:137-160 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ፍርድህም ትክክል ነው። ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤ እጅግ አስተማማኝም ነው። ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣ ቅናት አሳረረኝ። ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤ ባሪያህም ወደደው። እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም። ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ ሕግህም እውነት ነው። መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው። ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤ በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ። ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤ ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ። ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ። ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣ ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል። እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤ ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህም ሁሉ እውነት ናቸው። ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው፣ ከጥንት ምስክርነትህ ተረድቻለሁ። ሕግህን አልረሳሁምና፣ ሥቃዬን ተመልከት፤ ታደገኝም። ተሟገትልኝ፤ አድነኝም፤ እንደ ቃልህም ሕያው አድርገኝ። ሥርዐትህን ስለማይሹ፣ ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ እንደ ሕግህ ሕያው አድርገኝ። የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከምስክርህ ዘወር አላልሁም። ቃልህን አይጠብቁምና፣ ከዳተኞችን አይቼ አርቃቸዋለሁ። መመሪያህን እንዴት እንደምወድድ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤ ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው።

መዝሙር 119:137-160 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፤ ፍርድህም ቅን ነው። ሕግህ በፍጹም እውነትና ትክክል ነው። ጠላቶቼ ትእዛዞችህን አለመቀበላቸው በጣም ያበሳጨኛል። የተስፋ ቃልህ እጅግ የታመነ ነው፤ እኔም በጣም እወደዋለሁ። እኔ የማልጠቅምና የተናቅሁ ብሆንም እንኳ ሥርዓትህን አልዘነጋሁም። ጽድቅህ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ሕግህም ዘለዓለማዊ እውነት ነው። ብዙ ችግርና ጭንቀት ደርሶብኛል፤ ትእዛዞችህ ግን ደስታን ይሰጡኛል። ሥርዓትህ ዘወትር ትክክል ነው፤ በሕይወት ለመኖር እንድችል ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! በሙሉ ልቤ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ስማኝ፤ እኔም ሕጎችህን እፈጽማለሁ። ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አድነኝም፤ እኔም ሕግህን እጠብቃለሁ። ጎህ ከመቅደዱ በፊት ርዳታህን በመፈለግ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በገባህልኝም ቃል ተስፋ አደርጋለሁ። ቃልህን በማሰላሰል ለማጥናት ሌሊቱን ሙሉ እነቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ስማኝ! በትእዛዝህ መሠረት ሕይወቴን ጠብቅ! ሕግህን የማያከብሩ፥ ክፉ ዕቅድ ዐቅደው የሚያሳድዱኝ ሰዎች ወደ እኔ ቀርበዋል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን ለእኔ ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህ ሁሉ እውነተኞች ናቸው። ሕጎችህን በማጥናት ለዘለዓለም እንዲጸኑ ያደረግሃቸው መሆናቸውን ከብዙ ጊዜ በፊት ተረድቼአለሁ። እኔ ሕግህን አልረሳሁም፤ ስለዚህ ችግሬን ተመልክተህ አድነኝ። ስለ መብቴ ተከራከርልኝ፤ አድነኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት በሕይወት አኑረኝ። ሕግህን ስለማይፈልጉ ክፉዎች የመዳን ተስፋ የላቸውም። እግዚአብሔር ሆይ! ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ በትእዛዝህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ! የሚጠሉኝና የሚያሳድዱኝ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህን ስለማይጠብቁ፥ ከሐዲዎችን አይቼ ተጸየፍኳቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ትእዛዞችህን እንደምወድ ተመልከት፤ ስለዚህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ በሕይወት አኑረኝ! ቃልህ በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ትክክለኛ ፍርድህም ዘለዓለማዊ ነው።

መዝሙር 119:137-160 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው። ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥ እጅግም ቅን ነው። ጠላቶቼ ቃልህን ረስተዋልና የቤትህ ቅንዓት አቀለጠኝ። ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፥ ባርያህም ወደደው። እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ግን አልረሳሁም። ጽድቅህ የዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ ቃልህም እውነት ነው። መከራና ችግር አገኙኝ፥ ትእዛዛትህ ግን ተድላዬ ናቸው። ምስክርህ ለዘለዓለም ጽድቅ ነው፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ በሕይወትም አኑረኝ። በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፥ ሥርዓትህን እፈልጋለሁ። ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አድነኝ፥ ምስክርህንም እጠብቃለሁ። ማለዳ ጮኽሁ፥ ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ። ቃልህን አስብ ዘንድ ዐይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ። አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ ድምፄን ስማ፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። በዓመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ፥ ከሕግህም ራቁ። አቤቱ፥ አንተ ቅርብ ነህ፥ መንገዶችህም ሁሉ ቅኖች ናቸው። ከዘለዓለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ጀምሮ ከምስክርህ የተነሣ አወቅሁ። ሕግህን አልረሳሁምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም። ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፥ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መድኃኒት ከኀጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና። አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፥ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፥ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም። ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ። ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፥ አቤቱ፥ በምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህም ፍርድ ሁሉ ለዘለዓለም ነው።