መዝሙር 119:113-136
መዝሙር 119:113-136 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ። የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ፣ እናንት ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር። ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ። መሠሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው። የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ ፍርድህንም እፈራለሁ። ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤ እብሪተኞች እንዲጨቍኑኝ አትፍቀድላቸው። ዐይኖቼ ማዳንህን፣ የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። እኔ ባሪያህ ነኝ፤ ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው። ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ ትእዛዞችህን ወደድሁ። መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች። የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣ አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም። ስምህን ለሚወድዱ ማድረግ ልማድህ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ። አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ። ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ። በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። ሕግህ ባለመከበሩ፤ እንባዬ እንደ ውሃ ይፈስሳል።
መዝሙር 119:113-136 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በፍጹም ልባቸው በአንተ የማይታመኑትን ወላዋዮች ሁሉ ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድኩ። አንተ ጋሻዬና መሸሸጊያዬ ነህ፤ በቃልህ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ፤ እኔ የአምላኬን ትእዛዞች መጠበቅ እፈልጋለሁ። በሕይወት እኖር ዘንድ በተስፋ ቃልህ መሠረት አበርታኝ! ተስፋዬንም አታጨልምብኝ! እድን ዘንድ ደግፈኝ፤ ሁልጊዜም ሕጎችህን እፈጽማለሁ። ዕቅዳቸው ተንኰልና ሐሰት የሞላበት በመሆኑ፥ ከሕግህ የሚያፈነግጡትን ሁሉ ታስወግዳቸዋለህ። ክፉዎችን ሁሉ እንደ ቆሻሻ ነገር ታስወግዳቸዋለህ፤ ስለዚህ ሥርዓትህን እወዳለሁ። አንተን ከመፍራቴ የተነሣ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርድህንም እጅግ ፈራሁት። ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር አድርጌአለሁ፤ ስለዚህ ለሚጨቊኑኝ ጠላቶቼ አትተወኝ! የእኔን የአገልጋይህን ደኅንነት አረጋግጥ፤ እብሪተኞች እንዲያጠቁኝ አታድርግ። አዳኝነትህንና እውነተኛ ቃል ኪዳንህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ። ለእኔ ለአገልጋይህ ፍቅርህን አሳይ፤ ሕጎችህንም አስተምረኝ። እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ ሥርዓትህንም እንዳውቅ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ ፍርድህን የምትገልጥበት ጊዜው አሁን ነው። ትእዛዞችህን ከወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ፤ አዎ፥ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ። የአንተ ትእዛዞች ትክክል መሆናቸውን ስለማምን የሐሰትን መንገድ ሁሉ እጠላለሁ። ሥርዓቶችህ አስደናቂዎች ናቸው፤ እኔም በሙሉ ልቤ እታዘዛቸዋለሁ። የቃልህ ትርጒም ብርሃን ይሰጣል፤ ሞኞችን አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዞችህን በጣም ከመናፈቄ የተነሣ አፌን በጒጒት እከፍታለሁ። ወደ እኔ ተመለስ፤ ለሚወዱህ ሁሉ እንደምታደርገውም ምሕረት አድርግልኝ። በተስፋ ቃልህ መሠረት አካሄዴን አስተካክል፤ ስሕተትም እንዲሠለጥንብኝ አታድርግ። ትእዛዞችህን መጠበቅ እንድችል ከሚጨቊኑኝ ሰዎች እጅ አድነኝ። የፊትህን ብርሃን ለባሪያህ አብራለት፤ ሕግህንም አስተምረኝ። ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ እንባዬ እንደ ወንዝ ውሃ ይፈስሳል።
መዝሙር 119:113-136 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግን ግን ወደድሁ። አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ። እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ፥ ከተስፋዬም አልፈር። እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ። ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው። የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኩሰት አጠፋሃቸው፥ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፥ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ። ፍርድንና ጽድቅን ሠራሁ፥ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ባርያህን በመልካም ጠብቀው፥ ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ። ዐይኖቼ ለማዳንህ፥ ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ። ለባርያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። እኔ ባርያህ ነኝ፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ምስክርህንም አውቃለሁ። ለጌታ የሥራ ጊዜ ነው፥ ሕግህንም ሻሩት። ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቁ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ። ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥ የዓመፅንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፥ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው። የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል። አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፥ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና። ስምህን ለሚወድዱ እንደምታደርገው ፍርድ፥ ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም። አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፥ ኃጢአትም ሁሉ አይግዛኝ። ከሰው ግፍ አድነኝ፥ ትእዛዝህንም እጠብቃለሁ። በባርያህ ላይ ፊትህን አብራ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዐይኖቼ ፈሰሰ።