መዝሙር 119:1-32

መዝሙር 119:1-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ብፁዓን ናቸው፤ መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ፤ ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔር ሕግ፤ ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት፤ ዐመፅን አያደርጉም፤ ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ። ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣ አንተ ሥርዐትን አዝዘሃል። ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣ ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ! ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያ ጊዜ አላፍርም። የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣ በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ ፈጽመህ አትተወኝ። ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣ በከንፈሬ እናገራለሁ። ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል። ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ። በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልዘነጋም። ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ ለአገልጋይህ መልካም አድርግ። ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት። እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር። ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ ነፍሴ እጅግ ዛለች። ከትእዛዞችህ የሳቱትን፣ እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ። ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣ ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ። ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣ አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል። ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤ መካሪዬም ነው። ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ። ነፍሴ በሐዘን ተዝለፈለፈች፤ እንደ ቃልህ አበርታኝ። የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ፤ ሕግህን በጸጋህ ስጠኝ። የእውነትን መንገድ መርጫለሁ፤ ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከምስክርነትህ ጋራ ተጣብቄአለሁ፤ አሳልፈህ ለውርደት አትስጠኝ። ልቤን አስፍተህልኛልና፣ በትእዛዞችህ መንገድ እሮጣለሁ።

መዝሙር 119:1-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በአካሄዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው፥ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት የሚኖሩ ሰዎች የተባረኩ ናቸው። ትእዛዞቹን የሚጠብቁ፥ በሙሉ ልባቸውም የሚፈልጉት፥ የተባረኩ ናቸው። የማይሳሳቱና በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሕጎችህን ሰጥተኸናል፤ በታማኝነት እንድንታዘዛቸውም ነግረኸናል፤ ድንጋጌህን በመጠበቅ ታማኝ ለመሆን በብርቱ እመኛለሁ። ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ከአስተዋልኩ ኀፍረት ከቶ አይደርስብኝም። የሕግህን ፍጹምነት ባወቅሁ መጠን በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ስለምፈጽም ፈጽሞ አትተወኝ። ወጣቶች ሕይወታቸውን በንጽሕና መጠበቅ የሚችሉት ትእዛዞችህን በመፈጸም ነው። አንተን በሙሉ ልቤ ስለምፈልግህ ትእዛዞችህን እንዳላፈርስ ጠብቀኝ። አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ የአንተን ሕግ አስተምረኝ። አንተ የሰጠኸውን ሕግ ሁሉ መላልሼ አነባለሁ። የአንተን ትእዛዝ መፈጸም ብዙ ሀብት የማግኘትን ያኽል ያስደስተኛል። ሥርዓትህን አጠናለሁ፤ በምትመራኝ መንገድ ላይም አተኲራለሁ። በሕግህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። በሕይወት እንድኖርና የቃልህን ትምህርት እንድጠብቅ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ። በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት ማየት እንድችል ዐይኖቼን ክፈትልኝ። እኔ በምድር ላይ በእንግድነት የምኖረው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ትእዛዞችህን አትሰውርብኝ። ነፍሴ ሥርዓትህን ለማግኘት ሁልጊዜ በመናፈቅ ተጨነቀች። የተረገሙትንና ከትእዛዞችህ የሚያፈነግጡትን ትዕቢተኞች ትገሥጻለህ። እኔ ሕግህን ስለ ጠበቅሁ ስድባቸውንና ንቀታቸውን ከእኔ አርቅልኝ። መሪዎች ተሰብስበው በእኔ ላይ ቢዶልቱም እንኳ እኔ አገልጋይህ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። ትእዛዞችህ ያስደስቱኛል፤ መካሪዎቼም እነርሱ ናቸው። ተሸንፌ ትቢያ ላይ ወድቄአለሁ፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። አድራጎቴን ሁሉ ተናዘዝኩ፤ አንተም ሰማኸኝ፤ እንግዲህ ሕግህን አስተምረኝ። ሕግህን እንዳስተውል እርዳኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ። ሐዘን በርትቶብኛል፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ኀይሌን አድስልኝ። ሐሰትን ከእኔ አርቅልኝ፤ በቸርነትህም ሕግህን አስተምረኝ። ታማኝ ለመሆንና ሕግህን ለመጠበቅ ወስኜአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! በሕግህ ጸንቼአለሁ፤ እባክህ አታሳፍረኝ። ብዙ ማስተዋልን ስለ ሰጠኸኝ፤ ትእዛዞችህን በትጋት እፈጽማለሁ።

መዝሙር 119:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በመንገዳቸው እንከን የሌለባቸው፥ በጌታም ሕግ የሚመላለሱ ምስጉኖች ናቸው። ሕጉን የሚጠብቁ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፥ ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ። ሕጎችህን በሚገባ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ። ደንቦችህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ምነው በቀኑ። ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና። አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ። ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። ከአፍህ የሚወጡትን ፍርዶች ሁሉ በከንፈሮቼ ደገምኳቸው። በብልጽግና እንደሚደሰቱ ሁሉ በሕጎችህ መንገድ ደስ አለኝ። ደንቦችህን አሰላስላለሁ፥ መንገዶችህንም እመለከታለሁ። በድንጋጌዎችህ ደስ ይለኛል፥ ቃልህንም አልረሳም። ለአገስልጋይህ መልካም አድርግለት፤ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ። ዐይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ። እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፥ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። ፍርዶችህን ሁልጊዜ በመፈለግ ነፍሴ በናፍቆት ደቀቀች። ከትእዛዛትህ የሚያፈነግጡተን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ገሠጽህ። ሕግህን ጠብቄአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ። መስፍኖች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፥ አገልጋይህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር። ሕግህም ተድላዬ ነው፥ ደንቦችህም አማካሪዎቼ ናቸው። ነፍሴ ወደ አፈር ተጠጋች፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። መንገዶቼን ዘረዘርሁ፥ ሰማኸኝም፥ ደንቦችህን አስተምረኝ። የድንጋጌዎችህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ። ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ በዕንባ ተዋጠች፥ እንደ ቃልህ አጠንክረኝ። የሐሰትን መንገድ ከእኔ አርቅ፥ የሕግህንም ጸጋ ስጠኝ፥ የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥ ፍርድህንም አልረሳሁም። አቤቱ፥ ሕግህን ተጠጋሁ፥ አታሳፍረኝ። ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዞችህ መንገድ ሮጥሁ።

መዝሙር 119:1-32

መዝሙር 119:1-32 NASVመዝሙር 119:1-32 NASVመዝሙር 119:1-32 NASV