የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 106:31-48

መዝሙር 106:31-48 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ለዘላለም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። ደግሞም በመሪባ ውሃ አጠገብ እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ ሙሴም ከእነርሱ የተነሣ ተቸገረ፤ የእግዚአብሔርንም መንፈስ ስላስመረሩት፣ ሙሴ የማይገባ ቃል ከአንደበቱ አወጣ። እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት፣ ሕዝቦችን ከማጥፋት ወደ ኋላ አሉ፤ እንዲያውም ከሕዝቦቹ ጋር ተደባለቁ፤ ልማዳቸውንም ቀሠሙ፤ ጣዖቶቻቸውንም አመለኩ፤ ይህም ወጥመድ ሆነባቸው። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ። የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፣ ለከነዓን ጣዖታት የሠዉአቸውን፣ ንጹሕ ደም አፈሰሱ፤ ምድሪቱም በደም ተበከለች። በተግባራቸው ረከሱ፤ በድርጊታቸውም አመንዝሮች ሆኑ። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ ርስቱንም ተጸየፈ። ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጠላቶቻቸውም በላያቸው ሠለጠኑ። ጠላቶቻቸው ጨቈኗቸው፤ በሥልጣናቸውም ሥር አዋሏቸው። እርሱ ብዙ ጊዜ ታደጋቸው፤ እነርሱ ግን ዐመፃን የሙጥኝ አሉ፤ በኀጢአታቸውም ተዋረዱ። ሆኖም ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ፣ ጭንቀታቸውን ተመለከተ፤ ለእነርሱም ሲል ቃል ኪዳኑን ዐሰበ፤ እንደ ምሕረቱም ብዛት ከቍጣው ተመለሰ። የማረኳቸው ሁሉ፣ እንዲራሩላቸው አደረገ። አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ አድነን፤ ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እናቀርብ ዘንድ፣ አንተን በመወደስ እንጓደድ ዘንድ፣ ከሕዝቦች መካከል ሰብስበህ አምጣን። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ ሕዝብም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

መዝሙር 106:31-48 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ይህም አድራጎቱ ወደ ፊት ለሚከተለው ትውልድ ለዘለዓለም እንደ መልካም ሥራ ሆኖ ተቈጠረለት። በመሪባ ምንጮች አጠገብ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ በእነርሱም ምክንያት ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ። እጅግ አስመርረውት ስለ ነበር ሙሴ ራሱን ባለመቈጣጠር ተናገረ። እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት አሕዛብን አላጠፉም፤ እንዲያውም ከእነርሱ ጋር ተደባልቀው የኑሮ ሥርዓታቸውን ተከተሉ። የእግዚአብሔር ሕዝቦች የአሕዛብን ጣዖቶች አመለኩ፤ ይህም ለጥፋታቸው ምክንያት ሆነ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንትና በከነዓን አገር ለሚገኙ ጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እነርሱ ለከነዓን ጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በመግደል ንጹሕ ደም አፍስሰዋል፤ ምድሪቱም በደም ረከሰች። እነርሱ በሥራቸው ረከሱ፤ በክፉ ሥራቸውም እግዚአብሔርን ካዱ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተቈጣ፤ እጅግም ተጸየፋቸው። ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጠላቶቻቸውም ገዥዎቻቸው ሆኑ። በጠላቶቻቸው ተጨቊነው ፈጽሞ የእነርሱ ተገዢዎች ሆኑ። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ታድጎአቸዋል፤ እነርሱ ግን በእርሱ ላይ ማመፅን መረጡ፤ ስለዚህ ኃጢአታቸው ለውድቀታቸው ምክንያት ሆነ። ይህም ሁሉ ሆኖ እንደገና ወደ እግዚአብሔር በሚጮኹበት ጊዜ ይሰማቸው ነበር፤ ሥቃያቸውንም ይመለከት ነበር። እነርሱን ለማዳን ቃል ኪዳኑን ያስታውስ ነበር፤ ስለ ታላቅ ፍቅሩም ምሕረት ያደርግላቸው ነበር። የሚጨቊኑአቸው ሁሉ እንዲራሩላቸው አደረገ። እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! አድነን! ከመንግሥታት መካከል መልሰህ ወደ አገራችን አግባን፤ በዚያን ጊዜ እናመሰግንሃለን፤ ቅዱስ ስምህንም እናከብራለን። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን! ሕዝቡ ሁሉ አሜን አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመስግኑ።

መዝሙር 106:31-48 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፥ በእነርሱም የተነሣ ሙሴ ተበሳጨ፥ በከንፈሮቹም ያለማስተዋል ተናገረ። ጌታ እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፥ ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ። ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው። ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ፥ የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠዉአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች። በሥራቸው ረከሱ፥ በድርጊታቸውም አመነዘሩ። የጌታም ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ። በአሕዛብም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው። ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ። ብዙ ጊዜ አዳናቸው፥ እነርሱ ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በስሕተታቸውም ተዋረዱ። እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፥ ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ጽኑ ፍቅሩም ብዛት ተጸጸተ። በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው። ጌታ አምላካችን ሆይ፥ አድነን፥ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን። ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ፥ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።