የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 106:31-48

መዝሙር 106:31-48 NASV

ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ለዘላለም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። ደግሞም በመሪባ ውሃ አጠገብ እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ ሙሴም ከእነርሱ የተነሣ ተቸገረ፤ የእግዚአብሔርንም መንፈስ ስላስመረሩት፣ ሙሴ የማይገባ ቃል ከአንደበቱ አወጣ። እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት፣ ሕዝቦችን ከማጥፋት ወደ ኋላ አሉ፤ እንዲያውም ከሕዝቦቹ ጋር ተደባለቁ፤ ልማዳቸውንም ቀሠሙ፤ ጣዖቶቻቸውንም አመለኩ፤ ይህም ወጥመድ ሆነባቸው። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ። የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፣ ለከነዓን ጣዖታት የሠዉአቸውን፣ ንጹሕ ደም አፈሰሱ፤ ምድሪቱም በደም ተበከለች። በተግባራቸው ረከሱ፤ በድርጊታቸውም አመንዝሮች ሆኑ። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ ርስቱንም ተጸየፈ። ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጠላቶቻቸውም በላያቸው ሠለጠኑ። ጠላቶቻቸው ጨቈኗቸው፤ በሥልጣናቸውም ሥር አዋሏቸው። እርሱ ብዙ ጊዜ ታደጋቸው፤ እነርሱ ግን ዐመፃን የሙጥኝ አሉ፤ በኀጢአታቸውም ተዋረዱ። ሆኖም ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ፣ ጭንቀታቸውን ተመለከተ፤ ለእነርሱም ሲል ቃል ኪዳኑን ዐሰበ፤ እንደ ምሕረቱም ብዛት ከቍጣው ተመለሰ። የማረኳቸው ሁሉ፣ እንዲራሩላቸው አደረገ። አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ አድነን፤ ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እናቀርብ ዘንድ፣ አንተን በመወደስ እንጓደድ ዘንድ፣ ከሕዝቦች መካከል ሰብስበህ አምጣን። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ ሕዝብም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።