ምሳሌ 9:1-18

ምሳሌ 9:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጥበብ ለራስዋ ቤቷን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶዎችዋን አቆመች። ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋንም በማድጋዋ ጨመረች። ማዕድዋን አዘጋጀች። አገልጋዮችዋን ልካ በከፍተኛ ዐዋጅ ወደ ማዕድዋ ጠራች። እንዲህም አለች፦ “አላዋቂ የሆነ ወደ እኔ ይምጣ፤” አእምሮ የጎደላቸውንም እንዲህ አለች፦ “ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ የጠመቅሁላችሁን የወይን ጠጅም ጠጡ። ስንፍናን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በሕይወትም ትኖሩ ዘንድ ዕውቀትን ፈልጉ፥ በመረዳትም ዕውቀትን አቅኑ።” ክፉዎችን የሚያስተምር ለራሱ ውርደትን ይቀበላል፥ ኃጥእንም የሚገሥጽ ራሱን ያዋርዳል። ሰነፎችን አትገሥጽ እንዳይጠሉህ፥ ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል። ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ ጥበብንም ያበዛል፤ ጻድቅንም አስተምረው፥ ዕውቀትንም ያበዛል። የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ የቅዱሳንም ምክር ዕውቀት ነው፥ ሕግንም ማወቅ ለልብ ደግ ነው። በዚህ ሥርዐት ብዙ ዘመን ትኖራለህ፥ የሕይወትህም ዓመታት ይጨመሩልሃል። ልጄ ሆይ፥ ለራስህ ጠቢብ ብትሆን ለባልንጀራህም ጠቢብ ትሆናለህ፥ ክፉም ብትሆን ክፋትን ለብቻህ ትሸከማለህ። ሐሰትን የሚያዘጋጅ ሰው ነፋሳትን እንደሚያዘጋጅ ሰው ይመስላል። እርሱም የሚበርር ዎፍን እንደሚከተል ነው። የወይኑ ቦታ መንገዱን ተወ፤ የሚሰማራባትን መንገድ ዘነጋ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፥ ለጥም ወደ ተሠራች ምድርም ይሄዳል፤ የማያፈራና የማይጠቅም ገንዘብንም በእጁ ይሰበስባል። ሰነፍና ነዝናዛ፥ እንጀራንም ያጣች ሴት ኀፍረትን የማታውቅ ትሆናለች። በቤቷ ደጅ በአደባባይ በወንበር ላይ በግልጥ ተቀምጣ፥ በመንገድ የሚያልፉትን አካሄዳቸውንም ያቀኑትን ትጠራለች። ከእነርሱ ወገን ሰነፍ የሆነው ወደ እርሷ ይቀርባል። አእምሮ የጐደለውንም እንዲህ ብላ ታዝዘዋለች፦ “የተሸሸገ እንጀራን አሰማምረህ ዳስስ። ጣፋጭ የስርቆት ውኃንም ጠጣ፥” ነገር ግን እርሱ ከኀያላን ወገን በእርሷ ዘንድ የሚጠፉ እንዳሉ፥ የሲኦል ወጥመድም በቤቷ እንደሚገኝ አያውቅም። ነገር ግን ፈጥነህ ሂድ፥ በቦታዋም አትዘግይ፥ የባዕድን ውኃ እንደምትሻገር በዐይንህ ወደ እርሷ መመልከትን አታዘውትር። ከባዕድ ውኃ ራቅ፥ ብዙ ዘመን ትኖር ዘንድ ከባዕድ ምንጭ ውኃ አትጠጣ። የሕይወትህም ዓመታት ይጨመሩልሃል።

ምሳሌ 9:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ ሰባቱን ምሰሶዎቿንም ጠርባ አቆመች፤ ፍሪዳዋን ዐረደች፤ የወይን ጠጇን ጠመቀች፤ ማእዷንም አዘጋጀች። ሴት አገልጋዮቿንም ላከች፤ ከከተማዪቱም ከፍተኛ ቦታ ተጣራች። እርሷም ልበ ቢሶችን፣ “አላዋቂዎች ሁሉ ወደዚህ ኑ” ትላለች። “ኑ፤ ምግቤን ተመገቡ፤ የጠመቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። የአላዋቂነት መንገዳችሁን ተዉ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በማስተዋልም መንገድ ተመላለሱ።” ፌዘኛን የሚገሥጽ ሁሉ ስድብን በራሱ ላይ ያመጣል፤ ክፉውን ሰው የሚዘልፍ ሁሉ ውርደት ያገኘዋል። ፌዘኛን አትዝለፈው፤ ይጠላሃል፤ ጠቢብን ገሥጸው፤ ይወድድሃል። ጠቢብን አስተምረው፣ ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤ ጻድቁን ሰው አስተምረው፤ ዕውቀቱን ይጨምራል። “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። ዘመንህ በእኔ ምክንያት ይረዝማልና፤ ዕድሜም በሕይወትህ ላይ ይጨመርልሃል። ጠቢብ ብትሆን ጥበበኛነትህ ለራስህ ነው፤ ፌዘኛ ብትሆን የምትጐዳው ያው አንተው ነህ።” ጥበብ የለሽ ሴት ለፍላፊ ናት፤ እርሷም ስድና ዕውቀት የለሽ ናት። በቤቷ ደጃፍ ላይ ትጐለታለች፤ በከተማዪቱ ከፍተኛ ቦታ በመቀመጫ ላይ ትቀመጣለች። በዚያ የሚያልፉትን፣ መንገዳቸውን ይዘው የሚሄዱትን ትጣራለች። እርሷም ልበ ቢሶችን፣ “አላዋቂዎች ሁሉ ወደዚህ ኑ” ትላለች። “የስርቆት ውሃ ይጣፍጣል፤ ተሸሽገው የበሉት ምግብ ይጥማል።” እነርሱ ግን ሙታን በዚያ እንዳሉ፣ ተጋባዦቿም በሲኦል ጥልቀት ውስጥ እንደ ሆኑ አያውቁም።

ምሳሌ 9:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጥበብ ቤትዋን ሠራች፤ ሰባት ምሰሶዎችንም ለቤትዋ አቆመች። ላዘጋጀችውም ግብዣ ፍሪዳ ዐረደች፤ የጣፈጠ የወይን ጠጅም ጠመቀች፤ ገበታም ዘርግታ ማእድ ሠራች። ገረዶችዋም በከተማው ከፍተኛ ቦታ ላይ ቆመው፥ “ዕውቀት የጐደላችሁ ሰዎች ሁሉ ወደዚህ ኑ!” እያሉ እንዲጣሩ አደረገች፤ ሞኙንም ሰው እንዲህ ትለዋለች። “ና ያዘጋጀሁትን ምግብ ብላ! የጠመቅኩትንም የወይን ጠጅ ጠጣ! ዕውቀት ከጐደላቸው ሰዎች ተለይ! በሕይወትም ትኖራለህ፤ በማስተዋልም መንገድ ወደፊት ተራመድ።” ትዕቢተኛን ሰው ብታርመው ስድብን ታተርፋለህ፤ ክፉውን ሰው ብትገሥጸው ጒዳት ይደርስብሃል። ትዕቢተኛን ሰው ብታርመው ይጠላሃል፤ ጠቢብን ሰው ብታርመው ግን ይወድሃል። ጠቢብን አስተምረው፥ በይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤ ደግን ሰው አስተምረው፤ ዕውቀትን ይጨምራል። እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። በእኔ አማካይነት ዕድሜህ ይረዝማል፤ ለሕይወትህም ዓመቶች ይጨመራሉ። ጥበብ ቢኖርህ ጥቅሙ ለራስህ ነው፤ ፌዘኛ ብትሆን የምትጐዳው ራስህን ነው። ዕውቀትን ማጣት፥ እንደ ለፍላፊ፥ ምንም ነገር እንደማታውቅ ደንቈሮና ኀፍረተቢስ ሴት መሆን ነው። እርስዋ በቤትዋ በር ላይ ወይም በከተማው ከፍተኛ ቦታ ላይ ትቀመጣለች፤ ሥራቸውን በቅንነት እየሠሩ በመንገድ የሚያልፉትን ሁሉ እንዲህ እያለች ትጣራለች፦ “እናንተ ዕውቀት የጐደላችሁ ሰዎች ወደ እኔ ኑ!” ሞኙንም ሰው እንዲህ ትለዋለች፦ “ሰርቀው የሚጠጡት ውሃ ይጣፍጣል፤ ተሸሽገው የሚበሉትም እንጀራ ያስደስታል።” እርሱም ወደ ቤትዋ የሚሄዱ ሁሉ እንደሚሞቱና እስከ አሁንም ወደ ቤትዋ የገቡ ወደ ሙታን ዓለም ተሽቈልቊለው እንደወረዱ አያውቅም።

ምሳሌ 9:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች። ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን አዘጋጀች፥ ማዕድዋን አሰናዳች። ሴቶች አገልጋዮችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች፦ “አላዋቂ የሆነ በዚህ በኩል ይለፍ፥” አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች፦ “ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ ያጣፈጥኩትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።” ፌዘኛን የሚገሥጽ ለራሱ ስድብን ይቀበላል፥ ክፉንም የሚዘልፍ ኃፍረት ይገጥመዋል። ፌዘኛን አትገሥጽ እንዳይጠላህ፥ ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል። ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ ይበልጡን ጠቢብ ይሆናል፥ ጻድቅንም አስተምረው፥ ይበልጡን አዋቂ ይሆናል። የጥበብ መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። ዘመንህ በእኔ ይበዛልና፥ የሕይወትህም ዕድሜ ይጨመርልሃልና። ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፥ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ። (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።) ልጄ ለራስህ አዋቂ ብትሆን ለባልንጀራህም አዋቂ ትሆናለህ፥ ለራስህ ክፉ ብትሆን ግን ክፋትን ለብቻህ ትሸከማለህ። ሐሰትን የሚያዘጋጅ ሰው ነፋሳትን እንደሚገዛ ነው፥ የሚበርር ወፍንም እንደሚከተል ይመስላል። የወይኑ ቦታ መንገዱን ረስቷልና፥ የሚሠማራባትን መንገድ እንዲስት አድርጓልና፥ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፥ ለጥም ወደ ተሠራች አገር ይሄዳል፥ የማያፈራ የማይጠቅም ገንዘብንም በእጁ ይሰበስባል። አላዋቂ ሴት ሁከተኛ ናት፥ አሳብ የላትም፥ አንዳችም አታውቅም። በቤትዋ ደጅ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ በወንበር ላይ ትቀመጣለች፥ በመንገድ የሚያልፉትን አካሄዳቸውንም ያቀኑትን ለመጥራት፦ “አላዋቂ የሆነ በዚያ ይለፍ፥” አእምሮ የጐደለውንም እንዲህ አለች፦ “የስርቆት ውኃ ይጣፍጣል፥ የተሸሸገም እንጀራ ደስ ያሰኛል።” ነገር ግን እርሱ ሙታን ከዚያ እንዳሉ፥ ተጋብዦችዋም በሲኦል ጥልቀት ውስጥ እንዳሉ አያውቅም።