ምሳሌ 8:22-29
ምሳሌ 8:22-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር ለሥራው የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፥ ምድርን ሳይፈጥር አስቀድሞ ከዓለም በፊት ሠራኝ፥ ቀላያትን ሳይፈጥር፥ የውኃ ምንጮችም ሳይፈልቁ፥ ተራሮች ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፥ እግዚአብሔር ከሰማይ በታች የሚታደርባቸውን ሀገሮችንና ዳርቻዎችን ሳይፈጥር። ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ ዙፋኑን በነፋሳት ላይ ባጸና ጊዜ፥ ደመናትን በላይ ባጸና ጊዜ፥ የቀላያትን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ፥
ምሳሌ 8:22-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እግዚአብሔር ከቀድሞ ሥራዎቹ በፊት፣ የተግባሮቹ መጀመሪያ አድርጎ አመጣኝ፤ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ፣ ከጥንት ከዘላለም ተሾምሁ። ከውቅያኖሶች በፊት፣ የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው በፊት ተወለድሁ፤ ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ ከኰረብቶችም በፊት ተወለድሁ፤ ምድርን ወይም ሜዳዎቿን፣ ወይም ምንም ዐይነት የዓለም ትቢያን ከመፍጠሩ በፊት እኔ ተወለድሁ። ሰማያትን በዘረጋ ጊዜ፣ በውቅያኖስ ላይ የአድማስ ምልክት ባደረገ ጊዜ እኔ እዚያ ነበርሁ፤ ደመናትን በላይ ባጸና ጊዜ፣ የውቅያኖስን ምንጮች በመሠረተ ጊዜ፣ ለባሕር ድንበርን በከለለ ጊዜ፣ ውሆችም የእርሱን ትእዛዝ እንዳያልፉ፣ የምድርንም መሠረቶች ወሰን ባበጀ ጊዜ፣
ምሳሌ 8:22-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት ፈጠረኝ፤ ከጥንት ጀምሮ የሥራው ተቀዳሚ አደረገኝ። ዓለም ከመፈጠርዋ አስቀድሞ፥ ከዘመናት በፊት ተሾምኩ። የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው፥ ውቅያኖሶችም ከመገኘታቸው በፊት ተወለድኩ። ተራራዎችና ኰረብቶች ከመመሥረታቸው በፊት ተወለድኩ። እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ ከመፍጠሩ በፊት፥ ወይም የመጀመሪያው ዐፈር እንኳ ከመፈጠሩ በፊት ተወለድኩ። እግዚአብሔር ሰማይን በዘረጋ ጊዜ፥ ጠፈርንም ከውቅያኖሶች በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ እኔ እዚያ አብሬው ነበርኩ። ደመናትን በጠፈር ባኖረበት ጊዜ፥ የውቅያኖስን ምንጭ በከፈተ ጊዜ፥ የባሕር ውሃዎች ከተመደበላቸው ስፍራ በላይ ከፍ እንዳይሉ ባዘዛቸው ጊዜ፥ የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ እኔ እዚያ አብሬው ነበርኩ።
ምሳሌ 8:22-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። ከጥንቱ ከዘለዓለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር፥ የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር። ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥ ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥