መጽሐፈ ምሳሌ 8
8
የጥበብ ውዳሴ
1አንተስ ጥበብን አስተምር፥
ማስተዋል ትመልስልህ ዘንድ፤
2በተራሮች ጫፍ ላይ ናትና፥
በጎዳና መካከልም ትቆማለች።
3በኀያላን በሮች ትጠብቃለች፥
በመግቢያዉም ትመሰገናለች፥
4እናንተ ሰዎች እናንተን እለምናለሁ፥
ቃሌንም ለሰዎች ልጆች እናገራለሁ።
5እናንተ የዋሆች፥ ጥበብን አስተውሉ፤
እናንተም ሰነፎች፥ ዕውቀትን ገንዘብ አድርጉ፤
6የተወደደች ነገርን እናገራለሁና ስሙ፤
ከከንፈሮቼም ቅን ነገርን አወጣለሁ፤
7አንደበቴ እውነትን ታስተምራለችና፥
የሐሰት ከንፈሮችም በፊቴ የረከሱ ናቸውና።
8የአፌ ቃላት ሁሉ እውነት ናቸው፤
ጠማማና እንቅፋት በውስጣቸው የለም።
9በሚያውቁ ፊት ሁሉ የቀና ነው፥
ዕውቀትንም ለሚያገኙ ሰዎች የቀና ነው።
10ከብር ይልቅ ትምህርትን፥
ከተፈተነ ወርቅም ይልቅ ዕውቀትን ተቀበሉ።
11ዋጋው ብዙ ከሆነ ዕንቍ ጥበብ ትበልጣለችና፥
የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም።
12እኔ ጥበብ ምክርን አሳደርሁ፥
ዕውቀትንና ዐሳብንም እኔ ጠራሁ።
13እግዚአብሔርን የሚፈራ ዐመፃን ይጠላል፤
ጥልንና ትዕቢትን፥ ክፉ መንገድንም ይጠላል።
የክፉ ሰዎችንም ጠማማ መንገድ ጠላሁ።
14ምክርና ሥልጣን የእኔ ናቸው፤
ማስተዋል የእኔ ነው፥ ብርታትም የእኔ ነው።
15ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥
ሹማምቶችም እውነትን ይጽፋሉ።
16ታላላቆች በእኔ ይከብራሉ።
መኳንንት በእኔ ምድርን ይይዛሉ፥
17እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥
እኔንም የሚሹ ሞገስን ያገኛሉ።
18ብልጥግናና ክብር
ብዙ ሃብትና ጽድቅም በእኔ ዘንድ አሉ።
19ከወርቅና ከከበረ ዕንቍ ይልቅ እኔን መምረጥ ይሻላል፥
ፍሬዬም ከጠራ ብር ይሻላል።
20እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥
በፍርድ ጎዳና መካከልም እመላለሳለሁ፥
21ለሚወድዱኝ ሀብትን እከፍላቸው ዘንድ
ቤተ መዛግብታቸውንም በመልካም ነገር እሞላ ዘንድ።
የሚሆነውን ነገር በየቀኑ ብነግራችሁ
ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ቍጥር አስባለሁ።
22እግዚአብሔር ለሥራው የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፥#“ወለደኝ”
23ምድርን ሳይፈጥር አስቀድሞ ከዓለም በፊት ሠራኝ፥
24ቀላያትን ሳይፈጥር፥
የውኃ ምንጮችም ሳይፈልቁ፥
25ተራሮች ሳይመሠረቱ፥
ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፥
26እግዚአብሔር ከሰማይ በታች የሚታደርባቸውን
ሀገሮችንና ዳርቻዎችን ሳይፈጥር።
27ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥
ዙፋኑን በነፋሳት ላይ ባጸና ጊዜ፥
28ደመናትን በላይ ባጸና ጊዜ፥
የቀላያትን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥
29ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ
ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥
የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ፥
30እኔ ከእርሱ ጋር እሠራ ነበር፤
ደስም አሰኘው ነበር፥
በየዕለቱ ሁልጊዜ በፊቱ ደስ ይለኝ ነበር።
31ዓለምንም ፈጥሮ በፈጸመና ደስ ባለው ጊዜ፥
ደስታዬ በሰው ልጆች መካከል ነበር።
32አሁንም ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥
መንገዴን የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው።
33ጥበብን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥
ቸልም አትበሉት።
34የሚሰማኝ ሰው ብፁዕ ነው፥
መንገዴን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፥
ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥
የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ።
35መንገዶቼ የሕይወት መንገዶች ናቸውና።
እኔን ያገኘ ሕይወትን አገኘ፤
ፈቃዱም በእግዚአብሔር ዘንድ ይዘጋጃል።
36በእኔ ላይ በደልን የሚፈጽሙ ራሳቸውን ይበድላሉ፤
የሚጠሉኝም ሞትን ይወድዳሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ