ምሳሌ 6:30-35
ምሳሌ 6:30-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሚሰርቅ ሌባ ቢያዝ የሚደንቅ አይደለም፥ የተራበች ነፍሱን ሊያጠግብ ይሰርቃልና፤ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ገንዘቡን ሁሉ ይሰጣል። አመንዝራ ግን በአእምሮው ጉድለት፥ ነፍሱ የሚጠፋበትን ጥፋት ይሠራል። ቍስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም ለዘለዓለም አይደመሰስም። ባሏ ቅንዐትንና ቍጣን የተመላ ነውና፥ በፍርድ ቀን አይራራለትም። የጠብ ካሣ በምንም አይለወጥም፥ በገንዘብ ብዛትም አይታረቀውም።
ምሳሌ 6:30-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ ሰዎች አይንቁትም። በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ ከተያዘ ሰባት ዕጥፍ መክፈል አለበት። የሚያመነዝር ሰው ግን ልበ ቢስ ነው፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል። መደብደብና ውርደት ዕጣው ነው፤ ኀፍረቱም ከቶ አይወገድም። ቅናት የባልን ቍጣ ይቀሰቅሳልና፤ በሚበቀልበትም ጊዜ ምሕረት አያደርግም። ምንም ዐይነት ካሳ አይቀበልም፤ የቱንም ያህል ብዙ ቢሆን መማለጃን ዕሺ አይልም።
ምሳሌ 6:30-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሌባ በተራበ ጊዜ ምግብ ቢሰርቅ ለሰዎች አስገራሚ ነገር አይሆንም። ቢያዝም የቤቱን ሀብት ሁሉ የሚያሸጥ ቢሆን እንኳ ሰባት እጥፍ አድርጎ ይከፍላል። የምንዝር ተግባር የሚፈጽም ሰው ግን ማስተዋል የጐደለው ነው፤ ሕይወቱንም በከንቱ ያጠፋል። ውርደትና ድብደባ ይደርስበታል፤ ሁልጊዜም እንደ ተዋረደ ይኖራል። ቅናት የባልን ቊጣ ያነሣሣል፤ በሚበቀልበትም ጊዜ አይራራም። ምንም ዐይነት ካሳ መቀበል አይፈልግም፤ የስጦታም ብዛት ቊጣውን አያበርድለትም።
ምሳሌ 6:30-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፥ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል። ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮ የጐደለው ነው፥ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል። ቁስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም አይደመሰስም። ቅንዓት ለሰው የቁጣ ትኩሳት ነውና፥ በበቀልም ቀን አይራራለትምና። እርሱም ምንም ካሣ አይቀበልም፥ ስጦታም ብታበዛለት አይታረቅም።