መጽሐፈ ምሳሌ 6
6
1ልጄ ሆይ፥ ለወዳጅህ ዋስ ብትሆን፥
እጅህን ለባላጋራህ ትሰጣለህ፤
2የሰው ከንፈሩ ጽኑ ወጥመድ ነው፤
በአፉ ቃል ይጠፋል።
3ልጄ ሆይ፥ እኔ የማዝዝህን አድርግ፤ ራስህንም አድን፤
ስለ ወዳጅህ በክፉዎች እጅ ወድቀሃልና፤
ሰነፍ አትሁን፥ የተዋስኸውን ወዳጅህን አነሣሣው።
4ለዐይንህ እንቅልፍን፥ ለሽፋሽፍቶችህም ሸለብታን አትስጥ፤
5እንደ ሚዳቋ ከወጥመድ፥
እንደ ወፍም ከጭራ ወጥመድ ትድን ዘንድ።
6አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥
መንገዱንም ተመልክተህ ቅና።
ከእርሱም ይልቅ ብልህ ሁን።
7ጌታ ሳይኖረው፥ መሰማርያ ሳይኖረው፥ የሚያሠራውም ሳይኖረው፥
8መብሉን በበጋ ይሰበስባል፥
በመከርም ጊዜ በሰፊ ቦታ ያስቀምጣል።
# ቀጣዩ የንብ ምሳሌ በዕብ. የለም። ወይም ወደ ንብ ሂድ፥ ሠራተኛ እንደ ሆነች፥
መልካም ሥራንም እንደምትሠራ ዕወቅ፥
የደከመችበትንም ነገሥታትና ሌሎች ሰዎች ለጤንነት ይወስዱታል።
በሁሉም ዘንድ የተወደደች ናት፥ የከበረችም ናት።
በአካሏ ደካማ ናት፥ በሥራዋ ግን የጸናች ናት፥#“በሥራዋ ግን የጸናች ናት” የሚለው በግሪኩ የለም።
ጥበብን አክብራ አሳየች።
9አንተ ታካች እስከ መቼ ትተኛለህ?
ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?
10ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ትቀመጣለህ፥
ጥቂት ታሸልባለህ፥ ጥቂትም እጆችህን በደረትህ ታጥፋለህ፤
11እንግዲህ ድህነት እንደ ክፉ መልእክተኛ፥
ችግርም እንደ ደኅና ርዋጭ ይመጣብሃል።
ሰነፍ ባትሆን ግን ባለጸግነትህ እንደምንጭ ይመጣልሃል፤
ችግርም እንደ ክፉ ርዋጭ ከአንተ ይርቃል።
12ዓመፀኛና ሰነፍ የሆነ ሰው
ቀና ያልሆኑ መንገዶችን ይሄዳል፤
13በዐይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥
በጣቱ ጥቅሻ ያመለክታል፤
14ጠማማ ልቡ ሁልጊዜ ክፋትን ያስባል፤
እንደዚህም ያለ ሰው ጠብን በከተማ ላይ ይዘራል።
15ስለዚህ የማይድን ውድቀትና መመታት፥ ጥፋትም ድንገት ይደርስበታል፤
እግዚአብሔር በሚጠላቸው ሁሉ ደስ ይለዋልና፤
ስለ ነፍሱ ርኵሰትም ይደቅቃልና፥
16እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ናቸው፥
ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤
17ትዕቢተኛ ዐይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥
የጻድቁን ደም የምታፈስስ እጅ፥
18ክፉ ዐሳብን የሚያበቅል ልብ፥
ክፉዉን ለማድረግ ወዲህና ወዲያ የምትሮጥ እግር፥
19ሐሰተኛ ምስክርን የሚያቀጣጥል፥
በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።
ከዝሙት መራቅ እንደሚገባ
20ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ሕጎች ጠብቅ፥
የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤
21ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፥
በአንገትህም እሰረው።
22ስትሄድም ይመራሃል፤
ከአንተም ጋር ይኖር ዘንድ ውሰደው።
ስትተኛ ይጠብቅሃል፤
ስትነሣም ያነጋግርሃል።
23ትእዛዝ መብራት፥ ሕግም ብርሃን ነውና፥
ትምህርትና ተግሣጽም የሕይወት መንገድ ነውና፥
24ከጐልማሳ ሚስት፥
ከሌላዪቱም አንደበት ነገረ ሠሪነት ትጠብቅህ ዘንድ ትእዛዜን ጠብቅ፥
25ውበቷ ድል አይንሣህ።
በዐይኖችዋ አትጠመድ፥ በቅንድቧም አትማረክ።
26የአመንዝራ ሴት ክብር እስከ አንዲት እንጀራ ነው፤
አመንዝራ ሴትም የተከበሩ ወንዶች ነፍስን ታጠምዳለች።
27በጕያው እሳትን የሚታቀፍ፥
ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?
28ወይም በፍም ላይ የሚሄድ፥
እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?
29ወደ ጐልማሳ ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤
የሚነካትም ሁሉ አይነጻም።
30የሚሰርቅ ሌባ ቢያዝ የሚደንቅ አይደለም፥
የተራበች ነፍሱን ሊያጠግብ ይሰርቃልና፤
31ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥
ነፍሱንም ያድን ዘንድ ገንዘቡን ሁሉ ይሰጣል።
32አመንዝራ ግን በአእምሮው ጉድለት፥
ነፍሱ የሚጠፋበትን ጥፋት ይሠራል።
33ቍስልንና ውርደትን ያገኛል፥
ስድቡም ለዘለዓለም አይደመሰስም።
34ባሏ ቅንዐትንና ቍጣን የተመላ ነውና፥
በፍርድ ቀን አይራራለትም።
35የጠብ ካሣ በምንም አይለወጥም፥
በገንዘብ ብዛትም አይታረቀውም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ