የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 5

5
ከዝሙት ስለ መራቅ
1ልጄ ሆይ፥ ጥበቤን ተመልከት፤
ጆሮህም ወደ ቃሌ ያድምጥ፥
2መልካም ዐሳብን ትጠብቅ ዘንድ
በከንፈሮቼ የማዝዝህን ዕወቅ።
3ከአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥
ወደ አመንዝራ ሴት አትመልከት፥
ለጊዜው ጕሮሮህን ያጣፍጣል፥
4ፍጻሜው ግን እንደ ሐሞት የመረረ ነው፥
ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅም የተሳለ ነው።
5እግሮችዋም ወደ ስንፍና ይወርዳሉ፥
አረማመድዋም ወደ ሞትና ወደ ሲኦል ያደርሳል።
ፍለጋዋ ከኀጢአት ቦታ አይርቅም፥
6በሕይወት መንገድም አትሄድም።
መሮጫዋ ሰንከልካላ ነው፥ የሚታወቅም አይደለም።
7አሁንም ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥
ቃሌንም የተናቀ አታድርግ
8መንገድህን ከእርስዋ አርቅ፥
ወደ ቤቷም ደጅ አትቅረብ፥
9ሕይወትህን ለሌላ እንዳትሰጥ፥
ንብረትህንም ምሕረት ለሌላቸው፤
10ባዕዳን በሀብትህ እንዳይጠግቡ፥
የድካምህም ፍሬ በባዕድ ሰው ቤት እንዳይገባ።
11ሰውነትህ በደከመ ጊዜ፥ ኋላ ትጸጸታለህ፥
12እንዲህም ትላለህ፦ “እንዴት ትምህርትን ጠላሁ!
ልቤም ከተግሣጽ እንዴት ራቀ!
13የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥
ጆሮዎቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም።
14በማኅበርና በጉባኤ መካከል፥
ወደ ክፉ ሁሉ ለመድረስ ጥቂት ቀረኝ።”
15ከማድጋህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ።
16ከምንጮችህ ውኆች ወደ ሜዳ አይፍሰሱ።#ምዕ. 5 ቍ. 16 በግእዝ በአዎንታ ነው።
ውኃዎችም ወደ አደባባዮች አይሂዱ፥
17ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥
ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ።
18የውኃ ምንጭህ ለአንተ ይሁንልህ፤
ከልጅነት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ።
19በዋሊያና በውርንጭላ ፍቅር፥
ከሚስትህ ጋር ተፋቀር፥
የፍቅርዋ ሞገስ ያርካህ፥ ለአንተ ትሁንህ፥
ሁልጊዜም ከአንተ ጋር ትኑር፤
በዚች ፍቅር ስትፋቀር ብዙ ትሆናለህ።
20ልጄ ሆይ፥#በዕብራይስጥ ብቻ። ከሌላዪቱ ሴት ጋር አትኑር፤
የአንተ ወዳልሆነችውም እጅህን አትዘርጋ።
21የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት ነውና፥
አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና።
22ኀጢአት ሰውን ያጠምዳል፥
ሁሉም በኀጢአቱ ልባብ ይታሰራል።
23እርሱ ከሰነፎች ጋር ይሞታል፤
ከስንፍናውም ብዛት የተነሣ ሕይወቱ ይጣላል፤
ስለ ስንፍናውም ይጠፋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ