የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ምሳሌ 6:20-32

ምሳሌ 6:20-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ሕጎች ጠብቅ፥ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፥ በአንገትህም እሰረው። ስትሄድም ይመራሃል፤ ከአንተም ጋር ይኖር ዘንድ ውሰደው። ስትተኛ ይጠብቅሃል፤ ስትነሣም ያነጋግርሃል። ትእዛዝ መብራት፥ ሕግም ብርሃን ነውና፥ ትምህርትና ተግሣጽም የሕይወት መንገድ ነውና፥ ከጐልማሳ ሚስት፥ ከሌላዪቱም አንደበት ነገረ ሠሪነት ትጠብቅህ ዘንድ ትእዛዜን ጠብቅ፥ ውበቷ ድል አይንሣህ። በዐይኖችዋ አትጠመድ፥ በቅንድቧም አትማረክ። የአመንዝራ ሴት ክብር እስከ አንዲት እንጀራ ነው፤ አመንዝራ ሴትም የተከበሩ ወንዶች ነፍስን ታጠምዳለች። በጕያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወይም በፍም ላይ የሚሄድ፥ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ጐልማሳ ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ አይነጻም። የሚሰርቅ ሌባ ቢያዝ የሚደንቅ አይደለም፥ የተራበች ነፍሱን ሊያጠግብ ይሰርቃልና፤ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ገንዘቡን ሁሉ ይሰጣል። አመንዝራ ግን በአእምሮው ጉድለት፥ ነፍሱ የሚጠፋበትን ጥፋት ይሠራል።

ምሳሌ 6:20-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ትእዛዝ አክብር፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው። ምንጊዜም በልብህ አኑራቸው፤ በዐንገትህም ዙሪያ እሰራቸው። በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤ በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤ በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል። እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ ይህችም ትምህርት ብርሃን፣ የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት፤ እርሷም ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ ልዝብ አንደበት ካላት ዘልዛላ ሴት ትጠብቅሃለች። ውበቷን በልብህ አትመኝ፤ በዐይኗም አትጠመድ፤ ጋለሞታ ሴት ቍራሽ እንጀራ ታሳጣሃለችና፤ አመንዝራዪቱም በሕይወትህ በራሱ ላይ ትሸምቃለች። ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን? አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣ በፍም ላይ መሄድ ይችላልን? ከሰው ሚስት ጋር የሚተኛም እንደዚሁ ነው፤ የሚደርስባትም ከቅጣት አያመልጥም። ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ ሰዎች አይንቁትም። በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ ከተያዘ ሰባት ዕጥፍ መክፈል አለበት። የሚያመነዝር ሰው ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል።

ምሳሌ 6:20-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ልጄ ሆይ! የአባትህን ትእዛዞች ፈጽም፤ እናትህ ያስተማረችህንም ከቶ አትተው፤ የእነርሱን መመሪያ ዘወትር ተከተል፤ ቃላቸውንም ዘወትር ጠብቅ፤ እነርሱም በጒዞህ ይመሩሃል፤ ስትተኛም ይጠብቁሃል፤ ስትነቃም ያነጋግሩሃል። የእግዚአብሔር ትእዛዝ፥ እንደ መብራት፥ ትምህርቱም እንደ ብርሃን ያበሩልሃል፤ ተግሣጹ እንዴት መኖር እንደሚቻል ያስተምራል። ከመጥፎ ሴት እንድትርቅና ከሌላ ሰው ሚስት አሳሳች ቃል እንድትጠበቅ ይረዱሃል። ቊንጅናዋን አትመኝ፤ በዐይንዋ ጥቅሻ አትማረክ። አንድ ወንድ ሴትኛ ዐዳሪዋን በአንድ እንጀራ ዋጋ ሊያገኛት ይችላል፤ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ማመንዘር ግን የሕይወት ዋጋ ያስከፍላል። በጉያው እሳት ይዞ ልብሱ የማይቃጠልበት ሰው አለን? እግሩስ ሳይቃጠል ፍም ረግጦ ለመሄድ የሚችል ሰው አለን? ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ግንኙነት የሚያደርግ እንደዚሁ ነው፤ የሌላውን ሰው ሚስት የሚነካ ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። ሌባ በተራበ ጊዜ ምግብ ቢሰርቅ ለሰዎች አስገራሚ ነገር አይሆንም። ቢያዝም የቤቱን ሀብት ሁሉ የሚያሸጥ ቢሆን እንኳ ሰባት እጥፍ አድርጎ ይከፍላል። የምንዝር ተግባር የሚፈጽም ሰው ግን ማስተዋል የጐደለው ነው፤ ሕይወቱንም በከንቱ ያጠፋል።

ምሳሌ 6:20-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፥ የእናትህንም ትምህርት አትተው፥ ሁልጊዜም በልብህ አኑራቸው፥ በአንገትህም እሰራቸው። ስትሄድም ይመሩሃል፥ ስትተኛ ይጠብቁሃል፥ ስትነሣ ያነጋግሩሃል። ትእዛዝ መብራት፥ ትምህርትም ብርሃን ነውና፥ የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነውና፥ ከክፉ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ ከሌላይቱም ሴት አታላይ ምላስ። ውበትዋን በልብህ አትመኘው፥ በዐይኖችዋም አትማረክ። የሴተኛ ዐዳሪዋ ዋጋ እስከ አንዲት እንጀራ ነው፥ አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች። በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? በፍም ላይ የሚሄድ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፥ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፥ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል። ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮ የጐደለው ነው፥ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል።