ምሳሌ 6:12-19
ምሳሌ 6:12-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ምናምንቴና ጨካኝ ሰው፣ ነውረኛ አንደበቱን ይዞ የሚዞር፣ በዐይኑ የሚጠቅስ፣ በእግሩ ምልክት የሚሰጥ፣ በጣቶቹ የሚጠቍም፣ በልቡ ተንኰል ክፋትን የሚያውጠነጥን፣ ምን ጊዜም ጠብ ይጭራል። ስለዚህ በቅጽበት መዓት ይወርድበታል፤ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም። እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦ ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈስሱ እጆች፣ ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣ በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።
ምሳሌ 6:12-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዓመፀኛና ሰነፍ የሆነ ሰው ቀና ያልሆኑ መንገዶችን ይሄዳል፤ በዐይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ጥቅሻ ያመለክታል፤ ጠማማ ልቡ ሁልጊዜ ክፋትን ያስባል፤ እንደዚህም ያለ ሰው ጠብን በከተማ ላይ ይዘራል። ስለዚህ የማይድን ውድቀትና መመታት፥ ጥፋትም ድንገት ይደርስበታል፤ እግዚአብሔር በሚጠላቸው ሁሉ ደስ ይለዋልና፤ ስለ ነፍሱ ርኵሰትም ይደቅቃልና፥ እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ናቸው፥ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዐይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ የጻድቁን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ ዐሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ክፉዉን ለማድረግ ወዲህና ወዲያ የምትሮጥ እግር፥ ሐሰተኛ ምስክርን የሚያቀጣጥል፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።
ምሳሌ 6:12-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ባለጌና ክፉ ሰው በየቦታው እየዞረ ነገር እያጣመመ ያወራል። እርሱም፥ ለማታለል በዐይኑ ይጠቅሳል፤ በእግሩ ያመለክታል፤ በእጁ ይጠቊማል። በጠማማ አእምሮው ዘወትር ክፉ ነገርን ለማድረግ ያቅዳል፤ ሁልጊዜ ጠብን ይዘራል። ስለዚህም በድንገት ጥፋት ይደርስበታል፤ ሊድን በማይችልበት ሁኔታ በቅጽበት ይወድማል። እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም እርሱ የሚጸየፋቸው ሰባት ሲሆኑ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፦ በንቀት የሚመለከት ዐይን፥ ሐሰትን የሚናገር ምላስ፥ ንጹሖች ሰዎችን የሚገድሉ እጆች፥ ክፉ ሐሳብ የሚያፈልቅ አእምሮ፥ ወደ ክፋት ለመሮጥ የሚቸኲሉ እግሮች፥ በውሸት ላይ ውሸት እየጨመረ የሚናገር ምስክር፥ በወዳጆች መካከል ጠብ የሚያነሣሣ ሰው።
ምሳሌ 6:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከንቱና ክፉ ሰው ጠማማ ንግግር ይዞ ይዞራል፥ በዓይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ያስተምራል፥ ጠማማነት በልቡ አለ፥ ሁልጊዜም ክፋትን ያቅዳል፥ ጠብንም ይዘራል። ስለዚህ ጥፋት ድንገት ይደርስበታል፥ ድንገት ይደቅቃል፥ ፈውስም ከቶ የለውም። ጌታ የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፋቸዋለች፥ ትዕቢተኛ ዐይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ አሳብን የሚያቅድ ልብ፥ ወደ ክፉ የሚሮጡ እግሮች፥ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።