ምሳሌ 6:1-35

ምሳሌ 6:1-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ልጄ ሆይ፥ ለወዳጅህ ዋስ ብትሆን፥ እጅህን ለባላጋራህ ትሰጣለህ፤ የሰው ከንፈሩ ጽኑ ወጥመድ ነው፤ በአፉ ቃል ይጠፋል። ልጄ ሆይ፥ እኔ የማዝዝህን አድርግ፤ ራስህንም አድን፤ ስለ ወዳጅህ በክፉዎች እጅ ወድቀሃልና፤ ሰነፍ አትሁን፥ የተዋስኸውን ወዳጅህን አነሣሣው። ለዐይንህ እንቅልፍን፥ ለሽፋሽፍቶችህም ሸለብታን አትስጥ፤ እንደ ሚዳቋ ከወጥመድ፥ እንደ ወፍም ከጭራ ወጥመድ ትድን ዘንድ። አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገዱንም ተመልክተህ ቅና። ከእርሱም ይልቅ ብልህ ሁን። ጌታ ሳይኖረው፥ መሰማርያ ሳይኖረው፥ የሚያሠራውም ሳይኖረው፥ መብሉን በበጋ ይሰበስባል፥ በመከርም ጊዜ በሰፊ ቦታ ያስቀምጣል። ወይም ወደ ንብ ሂድ፥ ሠራተኛ እንደ ሆነች፥ መልካም ሥራንም እንደምትሠራ ዕወቅ፥ የደከመችበትንም ነገሥታትና ሌሎች ሰዎች ለጤንነት ይወስዱታል። በሁሉም ዘንድ የተወደደች ናት፥ የከበረችም ናት። በአካሏ ደካማ ናት፥ በሥራዋ ግን የጸናች ናት፥ ጥበብን አክብራ አሳየች። አንተ ታካች እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ትቀመጣለህ፥ ጥቂት ታሸልባለህ፥ ጥቂትም እጆችህን በደረትህ ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነት እንደ ክፉ መልእክተኛ፥ ችግርም እንደ ደኅና ርዋጭ ይመጣብሃል። ሰነፍ ባትሆን ግን ባለጸግነትህ እንደምንጭ ይመጣልሃል፤ ችግርም እንደ ክፉ ርዋጭ ከአንተ ይርቃል። ዓመፀኛና ሰነፍ የሆነ ሰው ቀና ያልሆኑ መንገዶችን ይሄዳል፤ በዐይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ጥቅሻ ያመለክታል፤ ጠማማ ልቡ ሁልጊዜ ክፋትን ያስባል፤ እንደዚህም ያለ ሰው ጠብን በከተማ ላይ ይዘራል። ስለዚህ የማይድን ውድቀትና መመታት፥ ጥፋትም ድንገት ይደርስበታል፤ እግዚአብሔር በሚጠላቸው ሁሉ ደስ ይለዋልና፤ ስለ ነፍሱ ርኵሰትም ይደቅቃልና፥ እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ናቸው፥ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዐይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ የጻድቁን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ ዐሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ክፉዉን ለማድረግ ወዲህና ወዲያ የምትሮጥ እግር፥ ሐሰተኛ ምስክርን የሚያቀጣጥል፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ሕጎች ጠብቅ፥ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፥ በአንገትህም እሰረው። ስትሄድም ይመራሃል፤ ከአንተም ጋር ይኖር ዘንድ ውሰደው። ስትተኛ ይጠብቅሃል፤ ስትነሣም ያነጋግርሃል። ትእዛዝ መብራት፥ ሕግም ብርሃን ነውና፥ ትምህርትና ተግሣጽም የሕይወት መንገድ ነውና፥ ከጐልማሳ ሚስት፥ ከሌላዪቱም አንደበት ነገረ ሠሪነት ትጠብቅህ ዘንድ ትእዛዜን ጠብቅ፥ ውበቷ ድል አይንሣህ። በዐይኖችዋ አትጠመድ፥ በቅንድቧም አትማረክ። የአመንዝራ ሴት ክብር እስከ አንዲት እንጀራ ነው፤ አመንዝራ ሴትም የተከበሩ ወንዶች ነፍስን ታጠምዳለች። በጕያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወይም በፍም ላይ የሚሄድ፥ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ጐልማሳ ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ አይነጻም። የሚሰርቅ ሌባ ቢያዝ የሚደንቅ አይደለም፥ የተራበች ነፍሱን ሊያጠግብ ይሰርቃልና፤ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ገንዘቡን ሁሉ ይሰጣል። አመንዝራ ግን በአእምሮው ጉድለት፥ ነፍሱ የሚጠፋበትን ጥፋት ይሠራል። ቍስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም ለዘለዓለም አይደመሰስም። ባሏ ቅንዐትንና ቍጣን የተመላ ነውና፥ በፍርድ ቀን አይራራለትም። የጠብ ካሣ በምንም አይለወጥም፥ በገንዘብ ብዛትም አይታረቀውም።

ምሳሌ 6:1-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ልጄ ሆይ፤ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፣ ስለ ሌላውም ሰው እጅ መትተህ ቃል ብትገባ፣ በተናገርኸው ነገር ብትጠመድ፣ ከአፍህ በወጣውም ቃል ብትያዝ፣ ልጄ ሆይ፤ ራስህን ለማዳን ይህን አድርግ፤ በጎረቤትህ እጅ ስለ ወደቅህ፣ ሄደህ ራስህን አዋርድ፤ ጎረቤትህን አጥብቀህ ነዝንዘው። ዐይኖችህ እንቅልፍ አይያዛቸው፣ ሽፋሽፍቶችህም አያንጐላጁ። ከዐዳኝ እጅ እንዳመለጠች ሚዳቋ፣ ከአጥማጅ ወጥመድ እንዳፈተለከች ወፍ ራስህን አድን። አንተ ሰነፍ፤ ወደ ጕንዳን ሂድ፤ ዘዴውን አስተውለህ ጠቢብ ሁን፤ አዛዥ የለውም፤ አለቃም ሆነ ገዥ የለውም፤ ሆኖም ግን በበጋ ምግቡን ያከማቻል፤ በመከርም ወቅት ቀለቡን ይሰበስባል። አንተ ሰነፍ፤ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ማንቀላፋት፤ ጥቂት ማንጐላጀት፤ እጅን አጣጥፎ ጥቂት ጋደም ማለት፤ ድኽነት እንደ ወንበዴ፣ ዕጦትም መሣሪያ እንደ ታጠቀ ሰው ከተፍ ይልብሃል። ምናምንቴና ጨካኝ ሰው፣ ነውረኛ አንደበቱን ይዞ የሚዞር፣ በዐይኑ የሚጠቅስ፣ በእግሩ ምልክት የሚሰጥ፣ በጣቶቹ የሚጠቍም፣ በልቡ ተንኰል ክፋትን የሚያውጠነጥን፣ ምን ጊዜም ጠብ ይጭራል። ስለዚህ በቅጽበት መዓት ይወርድበታል፤ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም። እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦ ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈስሱ እጆች፣ ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣ በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው። ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ትእዛዝ አክብር፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው። ምን ጊዜም በልብህ አኑራቸው፤ በዐንገትህም ዙሪያ እሰራቸው። በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤ በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤ በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል። እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ ይህችም ትምህርት ብርሃን፣ የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት፤ እርሷም ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ ልዝብ አንደበት ካላት ባዕድ ሴት ትጠብቅሃለች። ውበቷን በልብህ አትመኝ፤ በዐይኗም አትጠመድ። ጋለሞታ ሴት ቍራሽ እንጀራ ታሳጣሃለችና፤ አመንዝራዪቱም በሕይወትህ በራሱ ላይ ትሸምቃለች። ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን? አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣ በፍም ላይ መሄድ ይችላልን? ከሰው ሚስት ጋራ የሚተኛም እንደዚሁ ነው፤ የሚደርስባትም ከቅጣት አያመልጥም። ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ ሰዎች አይንቁትም። በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ ከተያዘ ሰባት ዕጥፍ መክፈል አለበት። የሚያመነዝር ሰው ግን ልበ ቢስ ነው፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል። መደብደብና ውርደት ዕጣው ነው፤ ኀፍረቱም ከቶ አይወገድም። ቅናት የባልን ቍጣ ይቀሰቅሳልና፤ በሚበቀልበትም ጊዜ ምሕረት አያደርግም። ምንም ዐይነት ካሳ አይቀበልም፤ የቱንም ያህል ብዙ ቢሆን መማለጃን ዕሺ አይልም።

ምሳሌ 6:1-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ልጄ ሆይ! ዕዳውን ለመክፈል ለማይችል ሰው አንተ ልትከፍልለት ቃል ብትገባ፥ በተናገርከው ንግግር ብትጠመድ፥ በገባኸውም ቃል ብትያዝ፥ ልጄ ሆይ! በዚያ ሰው ሥልጣን ሥር ሆነሃል ማለት ነው፤ ስለዚህ ከእርሱ ቊጥጥር ነጻ ለመውጣት ብትፈልግ ፈጥነህ ወደ እርሱ ሂድ፤ ዋስትናውንም እንዲያወርድልህ ለምነው። ይህንን ሳታደርግ አትተኛ፤ በዐይንህም እንቅልፍ አይዙር። ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፥ ወፍ ከወጥመድ እንደሚያመልጡ አንተም ራስህን አድን። አንተ ሰነፍ ወደ ጒንዳን ሄደህ መንገድዋን ተመልክተህ ጥበብን ቅሰም። ጒንዳኖች መሪ፥ አለቃ፥ ወይም ገዢ የላቸውም፤ ነገር ግን በበጋ ወራት ምግባቸውን ያከማቻሉ፤ በመከር ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ይሰበስባሉ። ታዲያ፥ አንተ ሰነፍ! የምትተኛው እስከ መቼ ነው? ከእንቅልፍህስ የምትነቃው መቼ ነው? “ጥቂት እተኛለሁ፤ ጥቂት አንቀላፋለሁ፤ እጄንም አጣጥፌ ለጥቂት ጊዜ ዐርፋለሁ” ስትል፥ ገና ተኝተህ ሳለ ድኽነትና ማጣት የጦር መሣሪያ እንደ ታጠቀ ወንበዴ በድንገት ይደርሱብሃል። ባለጌና ክፉ ሰው በየቦታው እየዞረ ነገር እያጣመመ ያወራል። እርሱም፥ ለማታለል በዐይኑ ይጠቅሳል፤ በእግሩ ያመለክታል፤ በእጁ ይጠቊማል። በጠማማ አእምሮው ዘወትር ክፉ ነገርን ለማድረግ ያቅዳል፤ ሁልጊዜ ጠብን ይዘራል። ስለዚህም በድንገት ጥፋት ይደርስበታል፤ ሊድን በማይችልበት ሁኔታ በቅጽበት ይወድማል። እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም እርሱ የሚጸየፋቸው ሰባት ሲሆኑ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፦ በንቀት የሚመለከት ዐይን፥ ሐሰትን የሚናገር ምላስ፥ ንጹሖች ሰዎችን የሚገድሉ እጆች፥ ክፉ ሐሳብ የሚያፈልቅ አእምሮ፥ ወደ ክፋት ለመሮጥ የሚቸኲሉ እግሮች፥ በውሸት ላይ ውሸት እየጨመረ የሚናገር ምስክር፥ በወዳጆች መካከል ጠብ የሚያነሣሣ ሰው። ልጄ ሆይ! የአባትህን ትእዛዞች ፈጽም፤ እናትህ ያስተማረችህንም ከቶ አትተው፤ የእነርሱን መመሪያ ዘወትር ተከተል፤ ቃላቸውንም ዘወትር ጠብቅ፤ እነርሱም በጒዞህ ይመሩሃል፤ ስትተኛም ይጠብቁሃል፤ ስትነቃም ያነጋግሩሃል። የእግዚአብሔር ትእዛዝ፥ እንደ መብራት፥ ትምህርቱም እንደ ብርሃን ያበሩልሃል፤ ተግሣጹ እንዴት መኖር እንደሚቻል ያስተምራል። ከመጥፎ ሴት እንድትርቅና ከሌላ ሰው ሚስት አሳሳች ቃል እንድትጠበቅ ይረዱሃል። ቊንጅናዋን አትመኝ፤ በዐይንዋ ጥቅሻ አትማረክ። አንድ ወንድ ሴትኛ ዐዳሪዋን በአንድ እንጀራ ዋጋ ሊያገኛት ይችላል፤ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ማመንዘር ግን የሕይወት ዋጋ ያስከፍላል። በጉያው እሳት ይዞ ልብሱ የማይቃጠልበት ሰው አለን? እግሩስ ሳይቃጠል ፍም ረግጦ ለመሄድ የሚችል ሰው አለን? ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ግንኙነት የሚያደርግ እንደዚሁ ነው፤ የሌላውን ሰው ሚስት የሚነካ ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። ሌባ በተራበ ጊዜ ምግብ ቢሰርቅ ለሰዎች አስገራሚ ነገር አይሆንም። ቢያዝም የቤቱን ሀብት ሁሉ የሚያሸጥ ቢሆን እንኳ ሰባት እጥፍ አድርጎ ይከፍላል። የምንዝር ተግባር የሚፈጽም ሰው ግን ማስተዋል የጐደለው ነው፤ ሕይወቱንም በከንቱ ያጠፋል። ውርደትና ድብደባ ይደርስበታል፤ ሁልጊዜም እንደ ተዋረደ ይኖራል። ቅናት የባልን ቊጣ ያነሣሣል፤ በሚበቀልበትም ጊዜ አይራራም። ምንም ዐይነት ካሳ መቀበል አይፈልግም፤ የስጦታም ብዛት ቊጣውን አያበርድለትም።

ምሳሌ 6:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ልጄ ሆይ፥ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፥ ለእንግዳ ሰው ቃል ብትገባ፥ በአፍህ ቃል ከተጠመድህ፥ በአፍህ ቃል ከተያዝህ። ልጄ ሆይ፥ ይህን አድርግ ራስህንም አድን፥ በጎረቤትህ እጅ ወድቀሃልና፥ ፈጥነህ ሂድ፥ ጎረቤትህንም ነዝንዘው። ለዓይንህ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶችህም እንጉልቻን አትስጥ፥ እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፥ እንደ ወፍም ከአጥማጅ እጅ ትድን ዘንድ። አንተ ሰነፍ፥ ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብሏን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች። አንተ ሰነፍ፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት መተኛት፥ ጥቂት ማንቀላፋት፥ ለመተኛት ጥቂት እጅን ማጣጠፍ፥ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። ከንቱና ክፉ ሰው ጠማማ ንግግር ይዞ ይዞራል፥ በዓይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ያስተምራል፥ ጠማማነት በልቡ አለ፥ ሁልጊዜም ክፋትን ያቅዳል፥ ጠብንም ይዘራል። ስለዚህ ጥፋት ድንገት ይደርስበታል፥ ድንገት ይደቅቃል፥ ፈውስም ከቶ የለውም። ጌታ የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፋቸዋለች፥ ትዕቢተኛ ዐይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ አሳብን የሚያቅድ ልብ፥ ወደ ክፉ የሚሮጡ እግሮች፥ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፥ የእናትህንም ትምህርት አትተው፥ ሁልጊዜም በልብህ አኑራቸው፥ በአንገትህም እሰራቸው። ስትሄድም ይመሩሃል፥ ስትተኛ ይጠብቁሃል፥ ስትነሣ ያነጋግሩሃል። ትእዛዝ መብራት፥ ትምህርትም ብርሃን ነውና፥ የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነውና፥ ከክፉ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ ከሌላይቱም ሴት አታላይ ምላስ። ውበትዋን በልብህ አትመኘው፥ በዐይኖችዋም አትማረክ። የሴተኛ ዐዳሪዋ ዋጋ እስከ አንዲት እንጀራ ነው፥ አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች። በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? በፍም ላይ የሚሄድ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፥ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፥ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል። ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮ የጐደለው ነው፥ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል። ቁስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም አይደመሰስም። ቅንዓት ለሰው የቁጣ ትኩሳት ነውና፥ በበቀልም ቀን አይራራለትምና። እርሱም ምንም ካሣ አይቀበልም፥ ስጦታም ብታበዛለት አይታረቅም።