ምሳሌ 5:1-19
ምሳሌ 5:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጄ ሆይ፥ ጥበቤን ተመልከት፤ ጆሮህም ወደ ቃሌ ያድምጥ፥ መልካም ዐሳብን ትጠብቅ ዘንድ በከንፈሮቼ የማዝዝህን ዕወቅ። ከአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ ወደ አመንዝራ ሴት አትመልከት፥ ለጊዜው ጕሮሮህን ያጣፍጣል፥ ፍጻሜው ግን እንደ ሐሞት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅም የተሳለ ነው። እግሮችዋም ወደ ስንፍና ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሞትና ወደ ሲኦል ያደርሳል። ፍለጋዋ ከኀጢአት ቦታ አይርቅም፥ በሕይወት መንገድም አትሄድም። መሮጫዋ ሰንከልካላ ነው፥ የሚታወቅም አይደለም። አሁንም ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥ ቃሌንም የተናቀ አታድርግ መንገድህን ከእርስዋ አርቅ፥ ወደ ቤቷም ደጅ አትቅረብ፥ ሕይወትህን ለሌላ እንዳትሰጥ፥ ንብረትህንም ምሕረት ለሌላቸው፤ ባዕዳን በሀብትህ እንዳይጠግቡ፥ የድካምህም ፍሬ በባዕድ ሰው ቤት እንዳይገባ። ሰውነትህ በደከመ ጊዜ፥ ኋላ ትጸጸታለህ፥ እንዲህም ትላለህ፦ “እንዴት ትምህርትን ጠላሁ! ልቤም ከተግሣጽ እንዴት ራቀ! የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮዎቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም። በማኅበርና በጉባኤ መካከል፥ ወደ ክፉ ሁሉ ለመድረስ ጥቂት ቀረኝ።” ከማድጋህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ። ከምንጮችህ ውኆች ወደ ሜዳ አይፍሰሱ። ውኃዎችም ወደ አደባባዮች አይሂዱ፥ ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ። የውኃ ምንጭህ ለአንተ ይሁንልህ፤ ከልጅነት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። በዋሊያና በውርንጭላ ፍቅር፥ ከሚስትህ ጋር ተፋቀር፥ የፍቅርዋ ሞገስ ያርካህ፥ ለአንተ ትሁንህ፥ ሁልጊዜም ከአንተ ጋር ትኑር፤ በዚች ፍቅር ስትፋቀር ብዙ ትሆናለህ።
ምሳሌ 5:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጄ ሆይ፤ ጥበቤን ልብ በል፤ የማስተዋል ቃሌንም በጥሞና አድምጥ፤ ይህም ልባምነትን ገንዘብ እንድታደርግ፣ ከንፈሮችህም ዕውቀትን እንዲጠብቁ ነው። የአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ያንጠባጥባልና፤ አንደበቷም ከቅቤ ይለሰልሳል፤ በመጨረሻ ግን እንደ እሬት ትመርራለች፤ ሁለት አፍ እንዳለውም ስል ሰይፍ ትሆናለች። እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ፤ ርምጃዎቿም በቀጥታ ወደ ሲኦል ያመራሉ። ስለ ሕይወት መንገድ ደንታ የላትም፤ መንገዶቿ ዘወርዋራ ናቸው፤ ለርሷ ግን አይታወቃትም። እንግዲህ፣ ልጆቼ ሆይ፤ አድምጡኝ፤ ከምነግራችሁ ቃል ፈቀቅ አትበሉ። መንገድህን ከርሷ አርቅ፤ በደጃፏም አትለፍ፤ ይኸውም ጕብዝናህን ለሌሎች፣ ዕድሜህንም ለጨካኞች እንዳትሰጥ ነው፤ ባዕዳን በሀብትህ እንዳይፈነጥዙ፣ ልፋትህም የሌላውን ሰው ቤት እንዳያበለጽግ ነው። በዕድሜህ መጨረሻ ታቃሥታለህ፤ ሥጋህና ሰውነትህ ሲከዳህ። እንዲህም ትላለህ፤ “ምነው ተግሣጽን ጠላሁ! ልቤስ ምነው መታረምን ናቀ! የመምህሮቼን ቃል አልሰማሁም፤ አሠልጣኞቼንም አላደመጥኋቸውም፤ በመላው ጉባኤ ፊት፣ ወደ ፍጹም ጥፋት ተቃርቤአለሁ።” ከገዛ ማጠራቀሚያህ ውሃ፣ ከገዛ ጕድጓድህም የሚፈልቀውን ውሃ ጠጣ። ምንጮችህ ተርፈው ወደ ሜዳ፣ ወንዞችህስ ወደ አደባባይ ሊፈስሱ ይገባልን? ለአንተ ብቻ ይሁኑ፤ ባዕዳን አይጋሩህ። ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤ በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። እርሷ እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቋ ናት፤ ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ፤ ፍቅሯም ሁልጊዜ ይማርክህ።
ምሳሌ 5:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጄ ሆይ! እኔ ወደምነግርህ ጥበብና ማስተዋል አተኲረህ አድምጥ። ይህን ብታደርግ አስተዋይነት ይኖርሃል፤ ንግግርህም ዕውቀት እንዳለህ ይገልጣል፤ የአመንዝራ ሴት ከንፈር የማር ወለላ የሚያንጠባጥብ ይመስላል፤ ንግግርዋም ከዘይት ይልቅ የለዘበ ነው። በመጨረሻ ግን እርስዋ እንደ እሬት የመረረችና ሁለት አፍ እንዳለው ስለታም ሰይፍ የምትቈርጥ ነች። መንገዶችዋ ወደ ሞት የሚያደርሱ ናቸው፤ እርምጃዎችዋም ወደ ሲኦል ይመራሉ። ወደ ሕይወት በሚመራው መንገድ አትሄድም፤ እንዲሁ ትባዝናለች፤ መባዘንዋን ግን አታውቀውም። ልጄ ሆይ! አድምጠኝ፤ እኔም ከምነግርህ ትምህርት አትራቅ። እንደዚህች ካለችው ሴት ራቅ፤ ወደ ቤትዋ ደጃፍ እንኳ አትቅረብ። አለበለዚያ፥ አንተ የነበረህን ክብር ሌሎች ይወስዱታል፤ ገና በወጣትነትህ በጨካኞች ሰዎች እጅ ትገደላለህ፤ ሀብትህን ሁሉ ባዕዳን ሰዎች ይወስዱታል፤ የደከምክበትም ንብረት ለሌላ ሰው ይሆናል። ሁለንተናህ ተበልቶ ከማለቁ የተነሣ በሞት ጣዕር ተይዘሃል፥ እንዲህም ትላለህ፦ “የማልማረውና የሰውን ተግሣጽ የማልቀበለው ከቶ ለምንድን ነው! አስተማሪዎቼ የሚሉትን መስማት አልፈለግሁም፤ ምክራቸውንም አልተቀበልሁም። ስለዚህ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ መካከል ወደ ጥፋት ለመድረስ ተቃረብኩ።” ከራስህ ጒድጓድና ምንጭ ውሃ ጠጥተህ እንደምትረካ፥ ለሚስትህ ታማኝ በመሆንና እርስዋን ብቻ በመውደድ እርካ። ማንኛዋም ሴት የምትጠጣበት የውሃ ምንጭ አትሁን። ጒድጓድህና ምንጭህ ማንም ሰው ከአንተ ጋር የማይካፈላቸው የአንተ ብቻ ይሁኑ። ስለዚህ በወጣትነት ያገባሃት ሚስትህ እንደ ጥሩ የምንጭ ውሃ ስለ ሆነች ትባረክልህ፤ ከእርስዋም ጋር ደስ ይበልህ። እንደ ተወደደች ዋላ እንድ ተዋበችም ሚዳቋ ትሁንልህ፤ ውበትዋ ሁልጊዜ ያርካህ፤ በፍቅርዋም ዘወትር ደስ ይበልህ።
ምሳሌ 5:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጄ ሆይ፥ ጥበቤን አድምጥ፥ ጆሮህን ወደ ትምህርቴ አዘንብል፥ ጥንቃቄን ትጠብቅ ዘንድ ከንፈሮችህም እውቀትን እንዲጠብቁ። ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ አፍዋም ከዘይት የለዘበ ነውና፥ ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም፥ የተሳለ ነው። እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው፥ የቀና የሕይወትን መንገድ አታገኝም፥ በአካሄድዋ የተቅበዘበዘች ናት፥ የሚታወቅም አይደለም። አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ ከአፌም ቃል አትራቁ። መንገድህን ከእርሷ አርቅ፥ ወደ ቤትዋም ደጅ አትቅረብ፥ ክብርህን ለሌላ እንዳትሰጥ፥ ዕድሜህንም ለጨካኝ፥ ሌሎች ከኃይልህ እንዳይጠግቡ፥ ድካምህም ወደ ባዕድ ሰው ቤት እንዳይሄድ። በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ፥ ትላለህም፦ “እንዴት ትምህርትን ጠላሁ፥ ልቤም ዘለፋን ናቀ! የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም። በማኅበርና በጉባኤ መካከል ለክፉ ሁሉ ለመዳረግ ጥቂት ቀረኝ።” ከጉድጓድህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ። ምንጮችህ ወደ ሜዳ፥ ወንዞችህ ወደ አደባባይ ይፈስሳሉን? ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ። ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፥ ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ። እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ፥ ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ፥ በፍቅርዋም ሁልጊዜ ጥገብ።