ምሳሌ 4:20-27
ምሳሌ 4:20-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጄ ሆይ፥ ንግግሬን አድምጥ፤ ጆሮህንም ወደ ቃሌ አዘንብል። ምንጮችህ እንዳይደርቁ፥ በልብህ ጠብቃቸው። ለሚያገኙአቸው ሕይወት፥ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ናቸውና። ልብህን አጥብቀህ ጠብቅ፥ የሕይወት መገኛ ከእርሱ ነውና። ክፉ አፍን ከአንተ አርቅ፥ ሐሰተኞች ከንፈሮችንም ከአንተ አስወግድ። ዐይኖችህም አቅንተው ይዩ፥ ሽፋሽፍቶችህም ወደ እውነት ያመልክቱ። ለእግርህ ቀና መሄጃ ሥራ፥ መንገዶችህንም አቅና። ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከመጥፎ መንገድ መልስ። እግዚአብሔር የቀኝ መንገዶችን ያውቃልና፥ የግራ መንገዶች ግን ጠማሞች ናቸው። እርሱም መሄጃህን የቀና ያደርጋል፥ አካሄድህንም በሰላም ያሳምራል።
ምሳሌ 4:20-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጄ ሆይ፤ የምነግርህን አስተውል፤ ቃሌንም በጥንቃቄ አድምጥ። ከእይታህ አታርቀው፤ በልብህም ጠብቀው፤ ለሚያገኘው ሕይወት፤ ለመላው የሰው አካልም ጤንነት ነውና። ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና። ጥመትን ከአፍህ አስወግድ፤ ብልሹ ንግግርም ከከንፈሮችህ ይራቅ። ዐይኖችህ በቀጥታ ይመልከቱ፤ ትክ ብለህም ፊት ለፊት እይ። የእግርህን ጐዳና አስተካክል፤ የጸናውን መንገድ ብቻ ያዝ። ወደ ቀኝ ወደ ግራ አትበል፤ እግርህን ከክፉ ጠብቅ።
ምሳሌ 4:20-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጄ ሆይ! እኔ የምለውን አተኲረህ ስማ፤ ንግግሬንም በጥሞና አድምጥ። ከዐይንህ አታርቃቸው፤ በልብህም ውስጥ ጠብቃቸው። እነርሱም ለሚያስተውሉአቸው ሕይወትን፥ ለመላ ሰውነትም ጤንነትን ይሰጣሉ። ልብ የሕይወት ምንጭ ስለ ሆነ ልብህን ከሁሉ ነገር አስበልጠህ ጠብቀው። ክፉ ንግግር ከአፍህ አይውጣ፤ ሐሰትንና ማታለልን ከአንተ አርቃቸው። አመለካከትህ ቀጥተኛ ይሁን፤ ግራና ቀኝ ሳትል ወደፊት ተመልከት። እግሮችህ በቀና መንገድ ላይ ይራመዱ። መንገድህም ሁሉ ይቃናልሃል። አቅጣጫህን ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ አታድርግ፤ ወደ ክፉ ነገር ከመሄድ እግርህን መልስ።
ምሳሌ 4:20-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጄ ሆይ፥ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሎቼም ጆሮህን አዘንብል። ከዓይንህ አታርቃቸው፥ በልብህም ውስጥ ጠብቃቸው። ለሚያገኙአቸው ሕይወት፥ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና። ከሁሉ አስበልጠህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት ምንጭ እርሱ ነውና። ጠማማ ንግግርን ከአንተ አስወግድ፥ አሳሳች ቃሎችን ከአንተ አርቅ። ዐይኖችህ አቅንተው ይዩ፥ አተኩረው ፊት ለፊት ይመልከቱ። የእግርህን መንገድ አቅና፥ አካሄድህም ሁሉ ይጽና። ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፥ እግርህንም ከክፉ መልስ።