ምሳሌ 30:1-33
ምሳሌ 30:1-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የያቄ ልጅ የአጉር ቃል ይህ ነው፤ ይህ ሰው ለኢቲኤል፣ ለኢቲኤልና ለኡካል ተናገረ፤ “እኔ ከሰው ሁሉ ይልቅ ደነዝ ነኝ፤ ሰው ያለው ማስተዋል የለኝም። ጥበብን አልተማርሁም፤ ስለ ቅዱሱም ዕውቀት የለኝም። ወደ ሰማይ የወጣ፣ የወረደስ ማነው? ነፋስን በእጁ ሰብስቦ የያዘ ማነው? ውሆችንስ በመጐናጸፊያው የጠቀለለ ማነው? የምድርን ዳርቻዎች ሁሉ የወሰነ ማነው? ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል? የምታውቅ ከሆነ እስኪ ንገረኝ! “የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ እርሱ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻቸው ነው። በርሱ ቃል ላይ አንዳች አትጨምር፤ አለዚያ ይዘልፍሃል፤ ሐሰተኛም ያደርግሃል። “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሁለት ነገር እለምንሃለሁ፤ እነዚህንም ከመሞቴ በፊት አትከልክለኝ፤ ሐሰትንና ሐሰት መናገርን ከእኔ አርቅልኝ፤ ድኽነትንም ሆነ ብልጽግናን አትስጠኝ፤ ብቻ የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ። አለዚያ ግን ያለ ልክ እጠግብና እክድሃለሁ፤ ‘እግዚአብሔር ማን ነው?’ እላለሁ፤ ወይም ድኻ እሆንና እሰርቃለሁ፤ የአምላኬንም ስም አሰድባለሁ። “አገልጋይን በጌታው ፊት በክፉ አታንሣው፤ አለዚያ ይረግምህና ጕዳት ያገኝሃል። “አባቱን የሚረግም፣ እናቱን የማይባርክ ትውልድ አለ፤ ራሳቸውን ንጹሓን አድርገው የሚቈጥሩ፣ ሆኖም ከርኩሰታቸው ያልነጹ አሉ፤ ዐይናቸው ትዕቢተኛ የሆነ፣ አስተያያቸው ንቀት የሞላበት፣ ድኾችን ከምድር፣ ችግረኞችንም ከሰው ዘር መካከል ለማጥፋት፣ ጥርሳቸው ሰይፍ የሆነ፣ መንጋጋቸውም ካራ የሆነ አሉ። “አልቅት ሁለት ሴት ልጆች አሉት፤ ‘ስጡን! ስጡን!’ እያሉ ይጮኻሉ። “ፈጽሞ የማይጠግቡ ሦስት ነገሮች አሉ፤ ‘በቃኝን’ ከቶ የማያውቁ አራት ናቸው፤ እነርሱም መቃብር፣ መካን ማሕፀን፣ ውሃ ጠጥታ የማትረካ ምድር፣ ‘በቃኝ’ የማይል እሳት ናቸው። “በአባት ላይ የምታፌዝ ዐይን፣ የእናትንም ትእዛዝ የምትንቅ፣ የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጧታል፤ ጆፌ አሞሮችም ይበሏታል። “እጅግ የሚያስደንቁኝ ሦስት ነገሮች አሉ፤ የማላስተውላቸውም አራት ናቸው፤ የንስር መንገድ በሰማይ፣ የእባብ መንገድ በቋጥኝ፣ የመርከብ መንገድ በባሕር፣ የሰውም መንገድ ከሴት ልጅ ጋራ ናቸው። “የአመንዝራዪቱ መንገድ ይህ ነው፤ በልታ አፏን በማበስ፣ ‘ምንም የሠራሁት ጥፋት የለም’ ትላለች። “ምድር በሦስት ነገር ትናወጣለች፤ እንዲያውም መሸከም የማትችላቸው አራት ነገሮች ናቸው፤ ባሪያ ሲነግሥ፣ ሰነፍ እንጀራ ሲጠግብ፣ የተጠላች ሴት ባል ስታገባ፣ ሴት ባሪያ በእመቤቷ እግር ስትተካ። “በምድር ላይ አራት ነገሮች ትንንሽ ናቸው፤ ሆኖም እጅግ ጠቢባን ናቸው፤ ጕንዳኖች ደካማ ፍጥረታት ናቸው፤ ሆኖም ምግባቸውን በበጋ ያከማቻሉ። ሽኮኮዎች ዐቅመ ደካማ ናቸው፤ ሆኖም መኖሪያቸውን በቋጥኞች መካከል ይሠራሉ፤ አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤ ሆኖም ቅደም ተከተል ይዘው ይጓዛሉ፤ እንሽላሊት በእጅ ትያዛለች፤ ሆኖም በቤተ መንግሥት ትገኛለች። “አረማመዳቸው ግርማዊ የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም በሞገስ የሚጐማለሉ አራት ናቸው፤ ከአራዊት መካከል ኀይለኛ የሆነው፣ ከምንም ነገር ፊት ግንባሩን የማያጥፈው አንበሳ፤ ጐርደድ ጐርደድ የሚል አውራ ዶሮ፣ አውራ ፍየል፣ እንዲሁም በሰራዊቱ የታጀበ ንጉሥ ናቸው። “ተላላ ሆነህ ራስህን ከፍ ከፍ ካደረግህ፣ ወይም ክፉ ነገር ካቀድህ፣ እጅህን በአፍህ ላይ አድርግ። ወተት ሲናጥ ቅቤ እንደሚወጣው፣ አፍንጫን ሲያሹት እንደሚደማ፣ ቍጣን ማነሣሣትም ጥልን ይፈጥራል።”
ምሳሌ 30:1-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የማሳ አገር ሰው የያቄ ልጅ አጉር በጥሞና የተናገራቸው ንግግሮች የሚከተሉት ናቸው፦ “አምላክ ሆይ! ደክሜአለሁ፤ አምላክ ሆይ! ደክሜአለሁ፤ እንዴት ልቋቋመው እችላለሁ? ከሰውነት ደረጃ ወጥቼ እንደ እንስሳ ሆኛለሁ፤ ሰው ሊኖረው የሚገባው ማስተዋል የለኝም። ከቶ ጥበብን አልተማርኩም፤ ስለ እግዚአብሔር የማውቀው ምንም ነገር የለኝም። ወደ ሰማይ ወጥቶ የወረደ ማን ነው? ነፋስን በእጁ የጨበጠ፥ ውሃን በልብሱ የቋጠረ፥ የምድርን ዳርቻ ያጸና ማን ነው? የሰውዬው ስም ማነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል? ታውቅ እንደሆን ንገረኝ፤ “እግዚአብሔር የሚናገረው ቃል ሁሉ እውነት ነው፤ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻ ነው። እርሱ ያላለውን ብሎአል ብትል ይገሥጽሃል፤ ሐሰተኛ መሆንህንም ይገልጣል።” አምላክ ሆይ! ከመሞቴ በፊት የሚከተሉትን ሁለት ነገሮች እንዳትነሣኝ እለምንሃለሁ፦ ሰውን ከማታለልና ሐሰት ከመናገር ጠብቀኝ፤ የሚያስፈልገኝን ያኽል ምግብ ስጠኝ እንጂ ሀብታም ወይም ድኻ አታድርገኝ። ብዙ ሀብት ቢኖረኝ “እግዚአብሔር ማን ነው?” ብዬ አንተን እስከ መካድ እደርሳለሁ፤ ድኻ ብሆን ደግሞ እሰርቅ ይሆናል፤ በዚህም ሁኔታ የአንተን የአምላኬን ስም አሰድባለሁ። እንዳትረገምና መከራ ላይ እንዳትወድቅ አገልጋይን ባሳዳሪው ፊት አትንቀፈው። አባቶቻቸውን የሚሰድቡ፥ እናቶቻቸውንም የማያመሰግኑ ሰዎች አሉ። በጣም የረከሱ ሆነው ሳለ ንጹሕ የሆኑ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። በትዕቢት የተሞሉና ሰውን የሚንቁ ሰዎች አሉ። ጥርሳቸው እንደ ሰይፍ፥ መንጋጋቸው እንደ ካራ የሆኑ ድኾችንና ችግረኞችን በግፍ የሚበዘብዙ ሰዎች አሉ። አልቅት “ስጠኝ! ስጠኝ!” እያሉ የሚጮኹ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉአት፤ እንዲሁም ከቶ የማይጠግቡና በቃን የማይሉ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም፦ “መቃብር፥ መኻን ሴት፥ ዝናብ የሚያስፈልገው ደረቅ ምድርና ከቊጥጥር ውጪ የሆነ የእሳት ቃጠሎ” ናቸው። በአባቱ የሚያፌዝና እናቱ በምታረጅበት ጊዜ የሚንቃት ሰው የሸለቆ ቊራዎች ዐይኖቹን ጐጥጒጠው ያወጡታል፤ ጆፌ አሞራዎችም ይበሉታል። ላስተውላቸው የማልችል እጅግ ምሥጢር የሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው። እነርሱም፦ “በሰማይ የሚበር ንስር፥ በአለት ላይ የሚጐተት እባብ፥ በባሕር ላይ የሚጓዝ መርከብና ከሴት ጋር ፍቅር የያዘው ወንድ” ናቸው። የማትታመን ሚስት ሁኔታም እንዲሁ ነው፤ እርስዋ በባልዋ ላይ ታመነዝርና ንጹሕ ሰው በመምሰል “ምንም በደል አልፈጸምኩም” ትላለች። በሦስት ነገሮች ምክንያት ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ ልትታገሥም አትችልም፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም “ባሪያ ሲነግሥ፥ ቦዘኔ ሲጠግብ፥ የተጠላች ሴት ባል ስታገባና፥ ሴት ባሪያ እመቤትዋን ስትወርስ” የሚከሠቱ ሁኔታዎች ናቸው። በዓለም ላይ በብልኅነታቸው የታወቁ አራት ትንንሽ ፍጥረቶች አሉ፤ ጒንዳኖች፦ ጒንዳኖች ደካሞች ናቸው፤ ነገር ግን በበጋ ጊዜ ምግባቸውን ያከማቻሉ። ሽኮኮዎች፦ ሽኮኮዎች ብርቱዎች አይደሉም፤ ነገር ግን መኖሪያቸውን በአለቶች መካከል ይሠራሉ። አንበጦች፦ አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤ ነገር ግን ሁሉም በሥነ ሥርዓት ይጓዛሉ። እንሽላሊቶች፦ እንሽላሊቶች በእጅ ስለሚያዙ ቀላል ፍጥረቶች መስለው ቢታዩም፥ በቤተ መንግሥት እንኳ ሳይቀር በሁሉ ስፍራ ይገኛሉ። አረማመዳቸው አስደሳች የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም፥ በእንስሶች መካከል ብርቱ የሆኑና ከማንም ፊት የማይሸሹ አንበሶች፥ አውራ ፍየሎች፥ የሚንጐራደዱ አውራ ዶሮዎች፥ በሕዝቦቻቸው ፊት በክብር የሚታዩ ነገሥታት ናቸው። ሞኝነትህ ትምክሕተኛ እንድትሆን ቢያደርግህና ክፉ ነገር ለማድረግ ብታቅድ፥ ቆም ብለህ አስብ። ወተት ቢናጥ ቅቤ ያስገኛል፤ የሰው አፍንጫ ቢጠመዘዝ ይደማል፤ ቊጣ ቢነሣሣ ጠብን ያመጣል።
ምሳሌ 30:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የማሣ አገር ሰው የያቄ ልጅ የአጉር ቃል። ሰውየው ለኢቲኤልና ለኡካል እንደዚህ ይናገራል፦ እኔ በእውነት ከሰው ሁሉ ይልቅ ደንቆሮ ነኝ፥ የሰውም ማስተዋል የለብኝም። ጥበብንም አልተማርሁም፥ ቅዱሱንም አላወቅሁትም። ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው? የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ የጠራ ነው፥ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው። እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር። ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ፥ ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፥ ድህነትንና ሀብታምነትን አትስጠኝ፥ የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም፦ “ጌታስ ማን ነው?” እንዳልል፥ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ የአምላኬንም ስም እንዳላረክስ። እንዳይሰድብህ በደለኛም እንዳትሆን ባርያን በጌታው ፊት በሐሰት አትተች። አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማያመሰግን ትውልድ አለ። ለራሱ ንጹሕ የሆነ የሚመስለው ከርኩሰቱ ግን ያልጠራ ትውልድ አለ። በትዕቢት ከፍ ከፍ ያሉ ዐይኖች ያሉት፥ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ። ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ለማጥፋትና ለመጨረስ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ። አልቅት “ስጠን ስጠን” የሚሉ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉት። ሦስቱ የማይጠግቡ አራቱም፦ “በቃን” የማይሉ ናቸው፥ እነርሱም ሲኦልና የማትወልድ ማኅፀን፥ ውኃ የማትጠግብ ምድርና፦ “በቃኝ” የማትል እሳት ናቸው። በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዐይን የሸለቆ ቁራዎች ይጐጠጉጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል። ሦስት ነገር ይገርመኛል፥ አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም። እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥ የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥ የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ናቸው። የአመንዝራ ሴት መንገድም እንዲሁ ነው። በልታ አፍዋን የምታብስ፦ “አንዳች ክፉ ነገርም አላደረግሁም” የምትል። በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም። አገልጋይ በነገሠ ጊዜ፥ ሞኝ እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥ የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥ ሴት አገልጋይም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ። በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፥ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፥ ገብረ ጉንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ። ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥ ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ። አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፥ ሁላቸውም ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ። እንሽላሊት በእጅ ይያዛል፥ በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል። መልካም አረማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥ አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፥ የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥ ማንንም ፈርቶ የማይመለስ፥ በእንስቶች መካከል በድፍረት የሚራመድ አውራ ዶሮ፥ መንጋን የሚመራ አውራ ፍየል፥ በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚናገር ንጉሥ። ከፍ ከፍ በማለት የተሞኝህ እንደሆነ፥ ክፉም ያሰብህ እንደሆነ፥ እጅህን በአፍህ ላይ ጫን። ወተት መናጥ ቅቤን ያወጣል፥ አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣል፥ እንዲሁም ቁጣን መጐተት ጠብን ያመጣል።