ምሳሌ 3:21-35

ምሳሌ 3:21-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ልጄ ሆይ፥ ቸል አትበል ዐሳቤንና ምክሬን ጠብቅ፤ ነፍስህ ትድን ዘንድ፥ ለአንገትህም ሞገስ ይሆንህ ዘንድ። ለሥጋህ ፈውስ፥ ለአጥንትህም ጠገን ይሆንልሃል። በመንገድህም ሁሉ በመተማመን ትሄዳለህ፥ እግሮችህም አይሰነካከሉም። በተቀመጥህም ጊዜ አትፈራም፤ ብትተኛም መልካም እንቅልፍ ትተኛለህ። ከሚመጣብህም አስደንጋጭ ነገር፥ ከሚመጣውም የክፉዎች ሰዎች አደጋ አትፈራም፤ እግዚአብሔር በመንገድህ ሁሉ ይኖራልና፥ እግሮችህም እንዳይነዋወጡ ያቆማቸዋልና። ለተቸገረው ሰው በጎ ነገር ማድረግን ቸል አትበል፥ በእጅህ ያለውን ያህል ርዳው። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ፥ ወዳጅህን፦ “ሂድና ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው፥ ነገ የምትወልደውን አታውቅምና። እርሱ ተማምኖብህ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ፥ እንደገና በወዳጅህ ላይ ክፉ አታስብ፤ እርሱ በላይህ የሠራው ክፉ ነገር ከሌለ፥ ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ። ከክፉ ሰዎች ዘንድ ሽሙጥን ገንዘብ አታድርግ፥ በመንገዳቸውም አትቅና። ኀጢአተኛ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና፤ ከጻድቃንም ጋር አንድ አይሆንም። የእግዚአብሔር መርገም በክፉዎች ቤት ነው፥ በጻድቃን ቤት ግን በረከት አለ። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማቸዋል፤ ለትሑታን ግን ክብርን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሰነፎች ግን ውርደታቸውን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።

ምሳሌ 3:21-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ጥበብና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤ እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤ ለነፍስህ ሕይወት፣ ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ። ከዚያም መንገድህን ያለ ሥጋት ትሄዳለህ፤ እግርህም አይሰናከልም፤ ስትተኛ አትፈራም፤ ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል። ድንገተኛን መከራ፣ በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤ እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል። ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። አሁን በእጅህ እያለ፣ ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣ በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት። ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣ ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ። በክፉ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ። እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል። የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል። እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።

ምሳሌ 3:21-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ልጄ ሆይ! መልካም ጥበብንና አርቆ ማስተዋልን አጥብቀህ ያዝ፤ ከአንተም እንዲርቁ አታድርግ። እነርሱም ለአንተ ረጅምና የአማረ ሕይወትን ይሰጡሃል። በመንገድህ ያለ ፍርሀት ተማምነህ መሄድ ትችላለህ፤ ከቶም አትሰናከልም። በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤ ሌሊቱንም ሙሉ የሰላም እንቅልፍ ታገኛለህ። በክፉ ሰዎች ላይ በድንገት የሚደርስ አደጋና ጥፋት ይደርስብኛል ብለህ አትፍራ። እግዚአብሔር መታመኛህ ሆኖ በወጥመድም ከመያዝ ይጠብቅሃል። ርዳታ እንድታደርግለት ለሚገባው ሰው ዐቅምህ በሚፈቅድልህ መጠን በጎ ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። የተቸገረ ጐረቤትህን ዛሬውኑ መርዳት ሲቻልህ “እሺ ነገ” እያልክ አታመላልሰው። አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በሚኖረው ጐረቤትህ ላይ በተንኰል ክፉ ነገር ለማድረግ አታስብ። ምንም በደል ያላደረሰብህን ሰው ያለ ምክንያት አትክሰሰው። በግፈኞች ሰዎች አትቅና፤ ክፉ ሥራቸውንም አትከተል። እግዚአብሔር ክፉ አድራጊዎችን ይጠላል፤ ልበ ቅኖችን ግን አጥብቆ ይወዳቸዋል። እግዚአብሔር በክፉ ሰዎች ቤት እርግማንን ያመጣል፤ የደጋግ ሰዎችን ቤት ግን ይባርካል። እግዚአብሔር ፌዘኞችን ይንቃል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን መልካም ክብርን ያገኛሉ፤ ሞኞች ግን ውርደትን ይከናነባሉ።

ምሳሌ 3:21-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዐይኖችህ አይራቁ፥ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ። የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም። በተኛህ ጊዜ አትፈራም፥ ስትተኛም፥ እንቅልፍህ የጣፈጠ ይሆንልሃል። ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኀጥኣን ጥፋት አትፈራም፥ ጌታ መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና። ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን፥ ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ከማድረግ አትቆጠብ። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ፥ ወዳጅህን፦ “ሂድና ተመለስ፥ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ፥ በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ። እርሱ ክፉ ካልሠራብህ፥ ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ። በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በጌታ ፊት ርኩስ ነውና፥ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። የጌታ መርገም በክፉ ሰዎች ቤት ነው፥ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል። በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፥ ሞኞች ግን መዋረድን ይቀበላሉ።