መጽሐፈ ምሳሌ 3:21-35

መጽሐፈ ምሳሌ 3:21-35 መቅካእኤ

ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዐይኖችህ አይራቁ፥ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ። የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም። በተኛህ ጊዜ አትፈራም፥ ስትተኛም፥ እንቅልፍህ የጣፈጠ ይሆንልሃል። ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኀጥኣን ጥፋት አትፈራም፥ ጌታ መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና። ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን፥ ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ከማድረግ አትቆጠብ። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ፥ ወዳጅህን፦ “ሂድና ተመለስ፥ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ፥ በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ። እርሱ ክፉ ካልሠራብህ፥ ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ። በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በጌታ ፊት ርኩስ ነውና፥ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። የጌታ መርገም በክፉ ሰዎች ቤት ነው፥ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል። በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፥ ሞኞች ግን መዋረድን ይቀበላሉ።