ምሳሌ 25:1-28

ምሳሌ 25:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እነዚህ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዷቸው ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፦ ነገርን መሰወር ለእግዚአብሔር ክብሩ ነው፤ ነገርን ፈልፍሎ ማውጣት ግን ለነገሥታት ክብራቸው ነው። ሰማያት ከፍ ያሉ እንደ ሆኑ፣ ምድርም ጥልቅ እንደ ሆነች ሁሉ፣ የነገሥታትም ልብ እንደዚሁ አይመረመርም። ከብር ዝገትን አስወግድ፤ አንጥረኛውም ንጹሕ ነገር ያገኛል፤ ክፉን ከንጉሥ ፊት አርቅ፤ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች። በንጉሥ ፊት ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ በታላላቆች መካከል መገኘትም አይመርህ፤ በትልቅ ሰው ፊት ከሚያዋርድህ፣ ራሱ፣ “ወደዚህ ከፍ በል” ቢልህ ይሻላልና። በዐይንህ ያየኸውን ሁሉ፣ ወደ ፍርድ አደባባይ በችኰላ አታውጣው፤ ባልንጀራህ ካሳፈረህ፣ ኋላ ምን ይውጥሃል? ስለ ራስህ ጕዳይ ከባልንጀራህ ጋራ በምትከራከርበት ጊዜ፣ የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ፤ አለዚያ ይህን የሚሰማ ያሳፍርሃል፤ አንዴ የጠፋውን ስምህንም ፈጽሞ መመለስ አትችልም። ባግባቡ የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው። የጠቢብ ሰው ዘለፋ ለሚሰማ ጆሮ፣ እንደ ወርቅ ጕትቻ ወይም እንደ ጥሩ የወርቅ ጌጥ ነው። በመከር ጊዜ የበረዶ ቅዝቃዜ ለሰስ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ታማኝ መልእክተኛም ለላኩት እንደዚሁ ነው፤ የጌቶቹን መንፈስ ያሳርፋልና። የማይለግሰውን ስጦታ እቸራለሁ ብሎ ጕራ የሚነዛ ሰው፣ ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው። በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል፤ ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል። ማር ስታገኝ በልክ ብላ፤ ከበዛ ያስመልስሃል። ወደ ባልንጀራህ ቤት እግር አታብዛ፤ ታሰለቸውና ይጠላሃል። በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር፣ እንደ ቈመጥ፣ እንደ ሰይፍና እንደ ተሳለ ፍላጻ ነው። በመከራ ጊዜ በወስላታ ሰው መተማመን፣ በተበላሸ ጥርስና በሰለለ እግር እንደ መታመን ነው። ላዘነ ልብ የሚዘምር፣ በብርድ ቀን ልብሱን እንደሚያወልቅ፣ ወይም በሶዳ ላይ እንደ ተጨመረ ሖምጣጤ ነው። ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም ውሃ አጠጣው። ይህን በማድረግህም፣ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ፤ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይከፍልሃል። የሰሜን ነፋስ ዝናብ እንደሚያመጣ ሁሉ፣ ሐሜተኛ ምላስም ቍጡ ፊት ታስከትላለች። ከጨቅጫቃ ሚስት ጋራ በአንድ ቤት ከመኖር፣ በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል። ከሩቅ የሚመጣ መልካም ዜና፣ የተጠማችን ነፍስ እንደሚያረካ ቀዝቃዛ ውሃ ነው። ለክፉ ሰው የሚንበረከክ ጻድቅ፣ እንደ ደፈረሰ ምንጭ ወይም እንደ ተበከለ የጕድጓድ ውሃ ነው። ከመጠን በላይ ማር መብላት ጥሩ አይደለም፤ የራስንም ክብር መሻት አያስከብርም። ራሱን የማይቈጣጠር ሰው፣ ቅጥሯ እንደ ፈረሰ ከተማ ነው።

ምሳሌ 25:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እነዚህ ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፤ እነርሱም በእጅ የተጻፉት በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቤተ መንግሥት በነበሩ ሰዎች አማካይነት ነበር። እግዚአብሔር የምሥጢር አምላክ ስለ ሆነ እናከብረዋለን፤ ነገሥታትን የምናከብራቸው ነገሮችን መርምረው በመግለጣቸው ነው። ንጉሥ የሚያስበውን ማወቅ አትችልም፤ የንጉሥ አሳብ እንደ ሰማይ የመጠቀ እንደ ውቅያኖስ የጠለቀ ነው። ከብር ዝገትን አስወግድ፤ ከዚያ በኋላ አንጥረኛ ያሳምረዋል። ከንጉሥ ፊት ክፉ ሰዎችን አስወግድ፤ መንግሥቱም በፍትሕ ጸንታ ትኖራለች። በንጉሥ ፊት በምትቆምበት ጊዜ ዝነኛ ለመሆን አትሞክር፤ ወደ ታላላቅ ሰዎችም ደረጃ ከፍ ለማለት አትፈልግ። ከአንተ ለበለጠ ሰው ስፍራህን እንድትለቅ በሹም ፊት ተጠይቀህ ከምታፍር ይልቅ “ና ወደ ላይ ከፍ በል!” ብትባል ይሻልሃል። አንተ ከመሰከርክ በኋላ ሌላ ሰው ምስክርነትህ የተሳሳተ መሆኑን የገለጠ እንደሆን ስለምታፍር ስለ አየኸው ነገር ለመመስከር ፈጥነህ ወደ ሸንጎ አትሂድ። በአንተና በባልንጀራህ መካከል ክርክር ቢነሣ ከእርሱ ጋር ተወያይተህ አለመግባባትህን አስወግድ እንጂ የሌላን ሰው ምሥጢር አታውጣ። አለበለዚያ ምሥጢር የማትጠብቅ መሆንክን የሚያውቅ ሰው ያዋርድሃል፤ ሊለወጥ የማይችልም መጥፎ ስም ይሰጥሃል። በወቅቱ በትክክል የተነገረ ቃል በብር ጻሕል ላይ እንደ ተቀመጠ ወርቅ ውበት ይኖረዋል። ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆነ ሰው ብልኅ ሰው የሚሰጠው ተግሣጽ ከወርቅ ጉትቻ ወይም ከጥሩ ወርቅ ከተሠራ ጌጥ ይበልጥ የተወደደ ይሆንለታል። ቀዝቃዛ ውሃ በሙቀት ጊዜ የሚያረካውን ያኽል ታማኝ መልእክተኛም የላከውን ሰው ያረካል። የማይሰጠውን ነገር “እሰጣለሁ” እያለ የሚመካ ሰው ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው። በትዕግሥት ማግባባት ታላቅ ተቃውሞን ያበርዳል፤ መሪዎችን ሳይቀር በሐሳብ እንዲስማሙ ያደርጋል። ሲበዛ እንዳያስጠላህ ከሚያስፈልግህ በላይ ብዙ ማር. አትብላ፤ ወደ ጐረቤትህ ቤት አዘውትረህ አትሂድ፤ ሊሰለችህና ሊጠላህ ይችላል። በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር ሰው የሰይፍ፥ የዱላና የተሳለ ፍላጻ ያኽል ሊጐዳው ይችላል። በመከራ ጊዜ በማይታመን ሰው ላይ መደገፍ በተነቃነቀ ጥርስ እንደማኘክና በተሰበረ እግር እንደ መራመድ ያኽል ነው። ላዘነ ሰው መዝፈን፥ በብርድ ቀን ልብስ የማውለቅና በቊስል ላይ ሆምጣጤ የመጨመር ያኽል የከፋ ነው። ጠላትህ ቢርበው አብላው፤ ቢጠማውም አጠጣው፤ ይህን ብትፈጽም በኀፍረት እሳት እንዲቃጠል ታደርገዋለህ፤ ለአንተ ግን እግዚአብሔር የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል። የሰሜን ነፋስ ዝናብን እንደሚያመጣ ሐሜትም ቊጣን ማስከተሉ የተረጋገጠ ነው። ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር ይልቅ በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል። ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ዜናን መስማት የደከመው ሰው ቀዝቃዛ ውሃ ጠጥቶ የሚረካውን ያኽል ያስደስታል። የክፉን ሰው ጠባይ የሚወርስ ደግ ሰው የደፈረሰን ምንጭ ወይም የተመረዘን ኲሬ ይመስላል። ብዙ ማር. መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም ከሰው ክብርን ለማግኘት መፈለግ አያስከብርም። ቊጣህን መቈጣጠር ባትችል መከላከያ አጥር እንደሌላትና ለጠላት ተጋልጣ እንደምትገኝ ከተማ ትሆናለህ።

ምሳሌ 25:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እነኚህም የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የገለበጧቸው የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው። የእግዚአብሔር ክብር በምሥጥራዊ መንገድ ነገርን ማከናወን ነው፥ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው። እንደ ሰማይ ከፍታ እንደ ምድርም ጥልቀት የነገሥታት ልብ አይመረመርም። ከብር ዝገትን አስወግድ፥ ፈጽሞም ይጠራል። ከንጉሥ ፊት ክፉ ሰዎችን አርቅ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች። በንጉሥ ፊት አትመካ፥ በታላላቆችም ስፍራ አትቁም፥ ዐይኖችህ ባዩት በመኰንን ፊት ከምትዋረድ፦ “ወደዚህ ከፍ በል” ብትባል ይሻልሃልና። ባልንጀራህ ባሳፈረህ ጊዜ ኋላ እንዳትጸጸት ለሙግት ወደ ሽንጎ ፈጥነህ አትውጣ፥ ሙግትህን ከባልንጀራህ ጋር በቀጥታ ፈጽም፥ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥ የሚሰማ እንዳይነቅፍህ፥ ስምህንም ለሁልጊዜ እንዳያጠፋው፤ በአግባብ የተነገረ ቃል፥ በብር ፃሕል ላይ እንደተቀመጠ ወርቅ ነው። የሚሰማን ጆሮ የሚገሥጽ ጠቢባዊ ምክር፥ እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቁ ነው። ለላኩት የታመነ መልእክተኛ፥ በመከር ወራት ደስ እንዲሚያሰኝ የውርጭ ጠል ነው፥ የጌታውን ነፍስ ያሳርፋልና። ስለ ስጦታው በሐሰት የሚመካ ሰው ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው። በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፥ ገር ምላስ አጥንትን ይሰብራል። በጣም እንዳትጠግብና እንዳትተፋው፥ ማር ባገኘህ ጊዜ የሚበቃህን ብላ። እንዳይሰለቸውና እንዳይጠላህ፥ አዘውትረህ ወደ ባልንጀራህ ቤት አትሂድ። በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር እንደ መዶሻና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ቀስት ነው። ከሃዲን ሰው በመከራ ጊዜ መተማመን እንደ ተሰበረ ጥርስና እንደ ሰለለ እግር ነው። ባዘነ ሰው ላይ የሚዘምር፥ በብርድ ቀን ልብስን እንደሚገፍና በቁስልም ላይ ሆምጣጤ እንደሚጨምር ሰው ነው። ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፥ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና፥ ጌታም ይሸልምሃልና። የሰሜን ነፋስ ዝናብ ያመጣል፥ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል። ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል። የቀዘቀዘ ውኃ ለደረቀ ጉሮሮ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ምሥራች እንዲሁ ነው። በኀጥእ ፊት የሚወድቅ ጻድቅ እንደደፈረሰ ምንጭና እንደ ተበከለ ኩሬ ነው። ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፥ ክቡር ነገሮችን መፈለግ ግን የሚያስከብር ነው። ራሱን መቆጣጠር የማይችል ሰው፥ ቅጥር እንደሌለው እንደ ፈረሰ ከተማ ነው።