ምሳሌ 15:20-33
ምሳሌ 15:20-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሞኝ ሰው ግን እናቱን ይንቃል። ልበ ቢስ ሰው ቂልነት ያስደስተዋል፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ይከተላል። ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል። ሰው ተገቢ መልስ በመስጠት ደስታን ያገኛል፤ በወቅቱም የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው! ወደ ሲኦል ከመውረድ እንዲድን፣ የሕይወት መንገድ ጠቢቡን ሰው ወደ ላይ ትመራዋለች። እግዚአብሔር የትዕቢተኛውን ቤት ያፈርሰዋል፤ የመበለቲቱን ዳር ድንበር ግን እንዳይደፈር ይጠብቃል። እግዚአብሔር የክፉውን ሰው ሐሳብ ይጸየፋል፤ የንጹሓን ሐሳብ ግን ደስ ያሠኘዋል። ስስታም ሰው በቤተ ሰቡ ላይ ችግር ያመጣል፤ ጕቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል። የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል፤ የክፉ ሰው አፍ ግን ክፋትን ያጐርፋል። እግዚአብሔር ከክፉዎች ሩቅ ነው፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል። ብሩህ ገጽታ ልብን ደስ ያሰኛል፤ መልካም ዜናም ዐጥንትን ያለመልማል። ሕይወት ሰጪ የሆነውን ተግሣጽ የሚሰማ፣ በጠቢባን መካከል ይኖራል። ተግሣጽን የሚንቅ ራሱን ይንቃል፤ ዕርምትን የሚቀበል ግን ማስተዋልን ያገኛል። እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን መማር ነው፤ ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች።
ምሳሌ 15:20-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ብልኅ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሞኝ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል። ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች በሞኝነታቸው ይደሰታሉ፤ ብልኆች ግን ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋሉ። መልካም ምክርን ብትቀበል ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ ምክርን ባትቀበል ግን ምንም ነገር አይሳካልህም። ተገቢውን ቃል በተገቢው ቦታ መናገር እጅግ ያስደስታል። ብልኾች ወደ ላይ በሚያመራው በሕይወት መንገድ ይሄዳሉ እንጂ፥ ወደ ታች በሚያወርደው በሞት መንገድ አይሄዱም። እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ቤት ይደመስሳል፤ ባልዋ የሞተባትን ሴት ድንበር እንዳይገፋ ይጠብቃል። እግዚአብሔር ክፉ ሐሳብን ይጠላል፤ ንጹሕ በሆነ ቃል ግን ደስ ይለዋል። በማጭበርበር ትርፍ ለማግኘት ብትሞክር ቤተሰብህን በችግር ላይ ትጥላለህ፤ ጉቦ አትቀበል፤ ለረጅም ዘመንም ትኖራለህ። ደጋግ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፤ ክፉዎች ግን በችኰላ ክፉ ቃል ይናገራሉ። እግዚአብሔር ከክፉዎች የራቀ ነው፤ ደጋግ ሰዎች ሲጸልዩ ግን ይሰማቸዋል። በፈገግታ የተሞላ ፊት ልብን ያስደስታል፤ የምሥራች ቃልም አጥንትን ያለመልማል። ሕይወት የሚሰጥ ምክር የሚቀበል የጠቢባን ጓደኛ ይሆናል። ተግሣጽን የሚጠላ ራሱን ይጐዳል። ተግሣጽን የሚቀበል ግን ጥበብን ይጨምራል። እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን የሚሰጥ ትምህርት ነው፤ ክብርን ለማግኘት በቅድሚያ ትሑት መሆን ያስፈልጋል።
ምሳሌ 15:20-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፥ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል። ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፥ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል። ምክር ከሌለች የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፥ መካሮች በበዙበት ግን ይጸናል። ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፥ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው! በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል። ጌታ የትዕቢተኞችን ቤት ይነቅላል፥ የባልቴትን ዳርቻ ግን ያጸናል። የበደለኛ አሳብ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ናት፥ ያማረ ቃል ግን ጥሩ ነው። ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል፥ መማለጃን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል። የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል፥ የኀጥኣን አፍ ግን ክፋትን ያፈልቃል። ጌታ ከኀጥኣን ይርቃል፥ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል። የዐይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥ መልካም ወሬም አጥንትን ያለመልማል። የሕይወትን ተግሣጽ የሚሰማ ጆሮ በጠቢባን መካከል ይኖራል። ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፥ ዘለፋን የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል። ጌታን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፥ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።