ምሳሌ 12:1-28

ምሳሌ 12:1-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤ ተግሣጽን የሚጠላ ግን ሰነፍ ነው። የተሻለ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል። ዐመፀኛ ሰው ግን ቸል ይባላል። ከዐመፃ የማይርቅ ሰው ይጠፋል፤ የጻድቃን ሥር ግን አይነቀልም። ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ ክፉ ሴት ግን ነቀዝ እንጨትን እንደሚበላ እንዲዚሁ ባሏን ትጐዳለች። የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፤ ኃጥኣን ግን ሽንገላን ያስተምራሉ። የኃጥኣን ምክር ተንኮል ነው። የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል። ኀጢአተኛ በተገለበጠበት ይጠፋል፥ የጻድቃን ቤቶች ግን ጸንተው ይኖራሉ። የብልህ ሰው አንደበት በሰው ሁሉ ዘንድ ይመሰገናል፤ ልበ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል። ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል። ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኃጥኣን ምሕረት ግን አለመመጽወት ነው። ምድሩን የሚያርሳት ሰው እንጀራን ይጠግባል፤ ቦዘኔነትን የሚከተል ግን የአእምሮ ድህነትን ይሰበስባል። በወይን ግብዣ ራሱን ደስ የሚያሰኝ ሰው በሰውነቱ ውርደትን ያመጣል። የኃጥኣን ምኞት ክፋት ናት። የጻድቃን ሥር ግን የጸና ነው። ኀጢአተኛ ሰው በከንፈሩ ኀጢአት ወደ ወጥመድ ይወድቃል፤ ጻድቅ ግን ከእርሱ ያመልጣል። አስፍቶ የሚመለከት ሰው ብዙ ምሕረትን ያገኛል። ድንገት በበር የሚገናኝ ግን ነፍሳትን ያስጨንቃል። የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም የከንፈሩን ዋጋ ይቀበላል። የሰነፎች መንገድ በፊታቸው የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። ሰነፍ ቍጣውን በየቀኑ ይናገራል፤ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። ጻድቅ ሰው የተገለጠ እውነትን ያስተምራል፤ የክፉዎች ምስክርነት ግን ውሸት ነው። በሐሰት የሚመሰክሩ በሰይፍ ይገድላሉ፤ በአፋቸው ሰይፍ አለና። የጠቢባን ምላስ ግን የቈሰለውን ይፈውሳል። የጻድቃን ከንፈሮች ምስክርነትን ያቀናሉ፥ የሚቸኩል ምስክር ግን ክፉ አንደበት አለው። ክፉን በሚያስብ ልብ ውስጥ ማታለል አለ፤ ሰላምን የሚወዱ ግን ደስ ይላቸዋል፥ ጻድቅን ምንም ክፉ ነገር ደስ አያሰኘውም፤ ክፉዎች ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ሐሰተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። ብልህ ሰው የጥበብ መንበር ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን መርገምን ያገኛል። የተመረጡ ሰዎች እጅ ፈጥኖ ይገዛል፤ ሐሰተኞች ሰዎች ግን ለምርኮ ይሆናሉ። የሚያስደነግጥ ቃል የጻድቅ ሰው ልቡናን ያውካል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል። ራሱን የሚያውቅ ሰው ለራሱ ጻድቅ ነው፤ የክፉዎች ሥራ ግን መልካም አይደለም። የሚበድሉ ሰዎችን ክፉ ይከተላቸዋል፥ የኃጥኣን መንገዳቸውም ታስታቸዋለች። ታካች ሰው አድኖ አይዝም። ንጹሕ ሰው ግን ክቡር ሀብት ነው። በጽድቅ መንገድ ሕይወት አለ፥ ክፉን የሚያስቡ ሰዎች መንገዶች ግን ወደ ሞት ያወርዳሉ።

ምሳሌ 12:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤ መታረምን የሚጠላ ግን ደነዝ ነው። መልካም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኛል፤ ተንኰለኛውን ግን እግዚአብሔር ይፈርድበታል። ሰው በክፋት ላይ ተመሥርቶ ሊጸና አይችልም፤ ጻድቃን ግን ከቦታቸው አይነቃነቁም። መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሚስት ግን ዐጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት። የጻድቃን ሐሳብ ቀና ነው፤ የክፉዎች ምክር ግን ሸር አለበት። የክፉዎች ቃል ደም ለማፍሰስ ታደባለች፤ የቅኖች ንግግር ግን ይታደጋቸዋል። ክፉ ሰዎች ይገለበጣሉ፤ ድራሻቸውም ይጠፋል፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ ጠማማ ልብ ያላቸው ግን የተናቁ ናቸው። የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል። ጻድቅ ሰው ለእንስሳቱ ይራራል፤ ክፉዎች ራሩ ቢባል እንኳ ዞሮ ዞሮ ሥራቸው ጭካኔ ነው። መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ ከንቱ ተስፋን የሚያሳድድ ግን ልበ ቢስ ነው። ኃጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤ የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል። ክፉ ሰው በክፉ ንግግሩ ይጠመዳል፤ ጻድቅ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል። ሰው ከከንፈሩ ፍሬ የተነሣ በበጎ ነገር ይሞላል፤ እንደ እጁ ሥራም ተገቢውን ዋጋ ያገኛል። ቂል ሰው መንገዱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ምክር ይሰማል። ቂል ሰው ቍጣው ወዲያውኑ ይታወቅበታል፤ አስተዋይ ሰው ግን ስድብን ንቆ ይተዋል። ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል። ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል። እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው። ክፋትን በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ አታላይነት አለ፤ ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቃን ጕዳት አያገኛቸውም፤ ክፉዎች ግን በመከራ የተሞሉ ናቸው። እግዚአብሔር ሐሰተኛ ከንፈርን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ደስ ይለዋል። አስተዋይ ሰው ዕውቀቱን ይሰውራል፤ የሞኞች ልብ ግን ቂልነትን ይነዛል። ትጉህ እጆች ለገዥነት ሲያበቁ፣ የስንፍና ፍጻሜ ግን የባርነት ሥራ ነው። ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሠኘዋል። ጻድቅ ሰው ለወዳጁ መልካም ምክር ይሰጣል፤ የክፉዎች መንገድ ግን ወደ ስሕተት ይመራቸዋል። ሰነፍ ዐድኖ ያመጣውን እንኳ አይጠብስም፤ ትጉህ ሰው ግን ለንብረቱ ዋጋ ይሰጣል። በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ፤ በዚያ ጐዳና ላይ ሞት የለም።

ምሳሌ 12:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዕውቀትን የሚወድ ሰው ከስሕተት መታረምን ይወዳል፤ ተግሣጽን የሚጠላ ግን ጅል ሰው ነው። ደግ ሰው ከእግዚአብሔር ሞገስን ያገኛል፤ ክፉ ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች ግን እርሱ ይፈርድባቸዋል። ማንም ሰው በክፋት ጸንቶ ሊቆም አይችልም። የእውነተኞች ሰዎች መሠረት ግን አይናወጥም አስተዋይ ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ ባልዋን የምታሳፍር ሴት ግን አጥንትን እንደሚያደቅ በሽታ ናት። እንደሚጐዳ ነቀርሳ በሽታ ትሆንበታለች። የእውነተኞች ሰዎች ሐሳብ የቀና ነው፤ የክፉዎች ምክር ግን አታላይነት ነው። ክፉዎች ሰውን ለማጥፋት በንግግራቸው ያጠምዳሉ፤ የቀጥተኞች ንግግር ግን ያድናቸዋል። ዐመፀኞች ወድቀው ደብዛቸው ይጠፋል የደጋግ ሰዎች ትውልድ ግን ጸንቶ ይኖራል። ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ አስተሳሰቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል። ሀብታም መስሎ በችግር ከሚኖር ሰው ይልቅ፥ ተራ ሰው መስሎ እየሠራ ኑሮውን የሚያሸንፍ ይሻላል። ደግ ሰው ለቤቱ እንስሳት ይራራል፤ የክፉ ሰው ርኅራኄ ግን ጭካኔ ነው። ትጉህ ገበሬ የተትረፈረፈ ምግብ ይኖረዋል፤ በከንቱ ምኞት መጠመድ ግን ሞኝነት ነው። የክፉ ሰዎች ምኞት ዘወትር ክፉ ነገርን ለማድረግ ነው፤ ደጋግ ሰዎች ግን እንደ መልካም ተክል መልካም ፍሬን ያፈራሉ። ክፉን ሰው የራሱ ክፉ ንግግር ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል። ደግ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል። የምታገኘው በረከት የመልካም ንግግርህና ሥራህ ውጤት ነው፤ በዚህ ዐይነት ተገቢ ዋጋህን ታገኛለህ። ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ሁልጊዜ ትክክል የሆኑ ይመስላቸዋል፤ ጠቢባን ግን መልካም ምክርን ይቀበላሉ። የሞኝ ቊጣ ወዲያው ይታወቃል፤ ብልኅ ሰው ግን በእርሱ ላይ የተሰነዘረውን ስድብ ችላ ይላል። እውነትን የሚናገር ሁሉ የታመነ ምስክርነትን ይሰጣል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ሰውን ያታልላል። ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቈስላል፤ በጥበብ የተነገረ ቃል ግን ይፈውሳል። እውነት ግን ጸንታ ትኖራለች። ሐሰት ዘላቂነት የለውም፤ ክፋትን በሚያቅዱ ሰዎች ልብ ተንኰል አለ፤ ሰላም የሚገኝበትን ነገር የሚመክሩ ግን ደስታን ያገኛሉ። ደጋግ ሰዎች ምንም ክፉ ነገር አይገጥማቸውም፤ ክፉዎች ግን መከራ ይበዛባቸዋል። የሚያተርፉት ነገር የለም። እግዚአብሔር ሐሰተኛ አንደበትን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ይደሰታል። አስተዋይ ሰዎች “ዐዋቂዎች ነን” እያሉ አይመጻደቁም፤ ሞኞች ግን “ዐዋቂዎች ነን” በማለት ድንቊርናቸውን ይገልጣሉ። በሥራ ትጉህ መሆን ገዢ ያደርጋል፤ ሰነፍ መሆን ግን ተገዢ ያደርጋል። በሐሳብ መጨነቅ ሐዘንን ያመጣል፤ በጎ ንግግር ግን ያስደስታል። እውነተኛ ሰው ወዳጁን በመምከር ወደ ቅን መንገድ ይመራዋል፤ የዐመፀኞች መንገድ ግን ከእውነት የሚያርቅ ነው። ሰነፍ ከሆንክ የምትመኘውን ማግኘት አትችልም፤ በትጋት ከሠራህ ግን ትበለጽጋለህ። እውነተኛነት የሕይወት መንገድ ነው፤ ክፋት ግን የሞት መንገድ ነው።

ምሳሌ 12:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፥ እርማትን የሚጠላ ግን ሞኝ ነው። መልካም ሰው ከጌታ ዘንድ ሞገስን ያገኛል፥ ተንኰለኛውን ሰው ግን ጌታ ይፈርድበታል። ክፋት ለሰው ዋስትና አያስገኝም፥ የጻድቃንን ሥር ግን ምንም አያንቀሳቅሰውም። ጐበዝ ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፥ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት። የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፥ የክፉዎች ምክር ግን ሽንገላ ነው። የክፉ ሰዎች ቃላት ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ የቅኖች አፍ ግን ያድናቸዋል። ክፉ ሰዎች ይወድቃሉ፥ ፈጽሞም አይገኙም፥ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፥ ልቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል። ምግብ ሳይኖረው ከሚኮራ ሰው አገልጋይ ኖሮት የተዋረደ ሰው ይሻላል። ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፥ የክፉ ሰው ርኅራኄ ግን ጭካኔ ነው። መሬቱን የሚቆፍር ሰው እንጀራ ይጠግባል፥ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን ማስተዋል የተሣነው ነው። ክፉ ሰዎች በክፉዎች ወጥመድ ይደሰታሉ፥ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል። ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፥ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል። የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል። የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፥ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። የሰነፍ ቁጣ ቶሎ ይታወቃል፥ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፥ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል። እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፥ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው። የእውነት ከንፈር ለዘለዓለም ትቆማለች፥ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው። ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፥ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቅን መከራ አያገኘውም፥ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ውሸተኛ ከንፈር በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፥ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል። የትጉ እጅ ትገዛለች፥ የታካች እጅ ግን ትገብራለች። ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፥ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል። ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፥ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች። ታካች ሰው አደን ምንም አያድንም፥ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው። በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ በጎዳናዋም ሞት የለም።