ምሳሌ 10:6-25

ምሳሌ 10:6-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው። የኃጥኣንን አፍ ግን ኀዘን በድንገት ይዘጋዋል። የጻድቃን መታሰቢያ ከምስጋና ጋር ነው። የኃጥኣን ስም ግን ይጠፋል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤ በከንፈሩ የማይታገሥ ግን በመሰናክል ይወድቃል። በየውሃት የሚሄድ ተማምኖ ይኖራል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። ለክፋት በዐይኑ የሚጠቃቀስ ለሰው ኀዘንን ይሰበስባል፥ በግልጽ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል። የሕይወት ምንጭ በጻድቃን አፍ ነው፥ የኃጥኣንን አፍ ግን ጥፋት ይከድነዋል። ቍጣ ጥልን ያነሣሣል። ፍቅር ግን የማይጣሉትን ሁሉ ይሸፍናቸዋል። ብልህ ሰው ከከንፈሩ ጥበብን ያወጣል፤ አእምሮ የጐደለውንም ሰው በበትር ይመታል። ጠቢብ ዕውቀትን ይሸሽጋል፤ የችኩል አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል። የባለጠጋ ሀብት የጸናች ከተማ ናት፤ የዕውቀት ድህነት ግን የኀጢአተኞች ጥፋት ነው። የጻድቃን ሥራ ሕይወትን ያደርጋል፤ የኃጥኣን ፍሬ ግን ኀጢአት ነው። ተግሣጽ የሕይወትን መንገድ ይጠብቃታል፤ በተግሣጽ የማይዘለፍ ግን ይስታል። ልዝብ ከንፈሮች ጥልን ይሸፍናሉ፤ ስድብን የሚያወጡ ግን ሰነፎች ናቸው። ኃጥእ ከነገር ብዛት የተነሣ ከኀጢአት አያመልጥም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው። የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፤ የኃጥኣን ልብ ግን ይጐድላል። የጻድቃን ከንፈሮች የሩቁን ያውቃሉ፤ ሰነፎች ግን በድህነት ይሞታሉ። የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ሆና ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ወደ ልብ አታመጣም። ሰነፍ ሰው በመሳቁ ክፉን ይሠራል፤ ጥበብ ግን ለሰው ዕውቀትን ትወልዳለች። ኃጥእ ወደ ጥፋት ይመለሳል፥ የጻድቅ ምኞቱ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደች ናት። ኃጥእ እንደ ዐውሎ ነፋስ ኅልፈት ይጠፋል፤ ጻድቅ ግን ተሰውሮ ለዘለዓለም ይድናል።

ምሳሌ 10:6-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል። የጻድቃን መታሰቢያቸው በረከት ነው፤ የክፉዎች ስም ግን እንደ ጠፋ ይቀራል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝ ይቀበላል፤ ለፍላፊ ቂል ግን ወደ ጥፋት ያመራል። ሐቀኛ ሰው ያለ ሥጋት ይራመዳል፤ በጠማማ ጐዳና የሚሄድ ግን ይጋለጣል። በተንኰለኛ ዐይን የሚጠቅስ ሐዘን ያስከትላል፤ ለፍላፊ ቂልም ወደ ጥፋት ያመራል። የጻድቅ አንደበት የሕይወት ምንጭ ናት፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል። ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤ ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል። ጥበብ በአስተዋይ ሰው ከንፈር ትገኛለች፤ በትር ግን ለልበ ቢስ ሰው ጀርባ ነው። ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ፤ የቂል አንደበት ግን ጥፋትን ይጋብዛል። የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ ድኽነት ግን የድኾች መጥፊያ ናት። የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤ የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች። ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል። ጥላቻውን የሚሸሽግ ሐሰተኛ አንደበት ያለው ነው፤ ሐሜትን የሚዘራ ሁሉ ሞኝ ነው። ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው። የጻድቅ አንደበት የነጠረ ብር ነው፤ የክፉ ሰው ልብ ግን ርባና የለውም። የጻድቃን ከንፈሮች ብዙዎችን ያንጻሉ፤ ቂሎች ግን በልበ ቢስነት ይሞታሉ። የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም። ሞኝ ሰው በክፉ ተግባር ይደሰታል፤ አስተዋይ ሰው ግን በጥበብ ደስ ይለዋል። ክፉ ሰው የፈራው ይደርስበታል፤ ጻድቅ የሚመኘው ይፈጸምለታል። ዐውሎ ነፋስ ሲነሣ ክፉዎች ተጠራርገው ይወሰዳሉ፤ ጻድቃን ግን ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።

ምሳሌ 10:6-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደግ ሰው በረከትን ያገኛል፤ ክፉ ሰው ግን ዐመፀኛነቱን በመልካም አነጋገር ይሸፍናል። የጻድቅ ሰው መታሰቢያ ለበረከት ይሆናል የክፉዎች ስም ግን ይጠፋል። በእውነት ጥበበኛ የሆነ ሰው ትእዝዞችን ይቀበላል፤ የሚለፈልፉ ሞኞች ግን ወደ ጥፋት ያመራሉ። በሁሉም ነገር ታማኝ ሰው ያለ ስጋት ይኖራል። የጠማማ ሰው እርምጃ ግን ይጋለጣል። በሰው ላይ መጠቃቀስ ችግርን ያመጣል፤ በግልጥ የሚነቅፍ ግን ሰላም እንዲገኝ ያደርጋል። የደግ ሰው ንግግር የሕይወት ምንጭ ነው፤ የክፉ ሰው ንግግር ግን የዐመፅ መሸፈኛ ነው። ጥላቻ ሁከትን ያነሣሣል፤ ፍቅር ግን በደልን ሁሉ አይታ በይቅርታ ታልፋለች። በአእምሮ የበሰሉ ሰዎች በማስተዋል ይናገራሉ። ሞኞች ግን ቅጣት መቀበል የሚገባቸው ናቸው። ጠቢባን በሚቻላቸው ዘዴ ሁሉ ዕውቀትን ያከማቻሉ፤ ሞኞች በሚናገሩበት ጊዜ ግን ጥፋት መምጣቱ አይቀርም። ባለጸጋን ሀብቱ እንደ ምሽግ ሆኖ ይጠብቀዋል፤ ድኻውን ግን ድኽነቱ ያጠፋዋል። የደግ ሰው መልካም ሥራ ሕይወትን ያስገኝለታል፤ የክፉ ሰው ኃጢአት ግን ቅጣትን ያስከትልበታል። ተግሣጽን የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ሕይወት መንገድ ያመራሉ፤ ከስሕተታቸው የማይማሩ ሰዎች ግን አደጋ ላይ ይወድቃሉ። ጥላቻውን የሚሸፍን ሰው ሐሰተኛ ነው፤ ሐሜትንም የሚያሠራጭ ሰው ሞኝ ነው። ከብዙ ንግግር ውስጥ ስሕተት አይጠፋም፤ ስለዚህ አስተዋይ ሰው ብዙ ከመናገር ይቈጠባል። የደግ ሰው ንግግር እንደ ነጠረ ብር ነው፤ የክፉ ሰው አሳብ ግን ዋጋቢስ ነው። የደግ ሰው ንግግር ብዙ ሰዎችን ይጠቅማል፤ ሞኞች ግን ከማስተዋል ጒድለት የተነሣ ይሞታሉ። የእግዚአብሔር በረከት ሐዘንን የማይጨምር ብልጽግና ይሰጣል። ስሕተት በማድረግ መደሰት ሞኝነት ነው፤ በአእምሮ የበሰሉ ሰዎች ደስ የሚላቸው ጥበብን በማግኘት ነው። ደጋግ ሰዎች የሚፈልጉትን ያገኛሉ፤ ክፉዎች ግን እጅግ የፈሩት ነገር ይደርስባቸዋል። ዐውሎ ነፋስ በሚነሣበት ጊዜ ክፉዎች ተጠርገው ይወሰዳሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን ዘወትር ጸንተው ይኖራሉ።

ምሳሌ 10:6-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፥ የክፉዎች አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፥ የክፉ ስም ግን ይጠፋል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፥ በከንፈሩ ሞኝ የሆነ ግን ይወድቃል። ያለ ነውር የሚመላለስ ተማምኖ ይሄዳል፥ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፥ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል። የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ማፍለቂያ ናት፥ የክፉዎች አፍ ግን ዐመፅን ይሸፍናል። ጥላቻ ክርክርን ታስነሣለች፥ ፍቅር ግን በደልን ሁሉ ትከድናለች። በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፥ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው። ጠቢባን እውቀትን ያከማቻሉ፥ የአላዋቂ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል። የሀብታም መዝገቡ የጸናች ከተማ ናት፥ የድሆች ውድቀት ድህነታቸው ነው። የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፥ የክፉ ገቢው ግን ለኃጢአት ነው። ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፥ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል። ጥላቻን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው፥ ሐሜትንም የሚገልጥ አላዋቂ ነው። በቃል ብዛት ውስጥ መተላለፍ ሳይኖር አይቀርም፥ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው። የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፥ የክፉ ልብ ግን ዋጋ ቢስ ነው። የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፥ አላዋቂዎች ግን ከማስተዋል ጉድለት የተነሣ ይሞታሉ። የጌታ በረከት ሀብታም ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርሷ ጋር አይጨምርም። ክፉ ነገር ማድረግ ለአላዋቂ ጨዋታ ነው፥ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው። የክፉ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፥ ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች። ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ክፉ ሰው አይገኝም፥ ጻድቅ ግን የዘለዓለም መሠረት ነው።