ምሳሌ 10:1-17
ምሳሌ 10:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ያሳዝናታል። የሀብት ድልብ ለኃጥኣን አይጠቅምም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች። እግዚአብሔር ጻድቅት ነፍስን አያስርብም፤ የኃጥኣንን ሕይወት ግን ከምድር ያስወግዳል። የሐኬተኛ እጅ ችግረኛ ያደርጋል፤ የትጉህ እጅ ግን ባለጠጋ ያደርጋል። የተማረ ልጅ ብልህ ይሆናል። ሰነፍ ልጅ ግን ራሱን ተገዥ ያደርጋል። ብልህ ልጅ ከቃጠሎ ይድናል፤ ኀጢአተኛ ልጅ ግን በአውድማ ነፋስ የሚጨብጥ ይሆናል። ብልህ ልጅ በመከር ጊዜ ይሠራል። ሰነፍ ልጅ ግን በመከር ጊዜ ይተኛል። የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው። የኃጥኣንን አፍ ግን ኀዘን በድንገት ይዘጋዋል። የጻድቃን መታሰቢያ ከምስጋና ጋር ነው። የኃጥኣን ስም ግን ይጠፋል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤ በከንፈሩ የማይታገሥ ግን በመሰናክል ይወድቃል። በየውሃት የሚሄድ ተማምኖ ይኖራል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። ለክፋት በዐይኑ የሚጠቃቀስ ለሰው ኀዘንን ይሰበስባል፥ በግልጽ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል። የሕይወት ምንጭ በጻድቃን አፍ ነው፥ የኃጥኣንን አፍ ግን ጥፋት ይከድነዋል። ቍጣ ጥልን ያነሣሣል። ፍቅር ግን የማይጣሉትን ሁሉ ይሸፍናቸዋል። ብልህ ሰው ከከንፈሩ ጥበብን ያወጣል፤ አእምሮ የጐደለውንም ሰው በበትር ይመታል። ጠቢብ ዕውቀትን ይሸሽጋል፤ የችኩል አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል። የባለጠጋ ሀብት የጸናች ከተማ ናት፤ የዕውቀት ድህነት ግን የኀጢአተኞች ጥፋት ነው። የጻድቃን ሥራ ሕይወትን ያደርጋል፤ የኃጥኣን ፍሬ ግን ኀጢአት ነው። ተግሣጽ የሕይወትን መንገድ ይጠብቃታል፤ በተግሣጽ የማይዘለፍ ግን ይስታል።
ምሳሌ 10:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሞኝ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል። ያላግባብ የተገኘ ሀብት አይጠቅምም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል። እግዚአብሔር ጻድቁ እንዲራብ አያደርግም፤ የክፉዎችን ምኞት ግን ያጨናግፋል። ሰነፍ እጆች ሰውን ያደኸያሉ፤ ትጉህ እጆች ግን ብልጽግናን ያመጣሉ። ሰብሉን በበጋ የሚሰበስብ ጠቢብ ልጅ ነው፤ በመከር ጊዜ የሚተኛ ግን ውርደት ይከተለዋል። በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል። የጻድቃን መታሰቢያቸው በረከት ነው፤ የክፉዎች ስም ግን እንደ ጠፋ ይቀራል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝ ይቀበላል፤ ለፍላፊ ቂል ግን ወደ ጥፋት ያመራል። ሐቀኛ ሰው ያለ ሥጋት ይራመዳል፤ በጠማማ ጐዳና የሚሄድ ግን ይጋለጣል። በተንኰለኛ ዐይን የሚጠቅስ ሐዘን ያስከትላል፤ ለፍላፊ ቂልም ወደ ጥፋት ያመራል። የጻድቅ አንደበት የሕይወት ምንጭ ናት፤ መዓት ግን የክፉዎችን አፍ ይዘጋል። ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤ ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል። ጥበብ በአስተዋይ ሰው ከንፈር ትገኛለች፤ በትር ግን ለልበ ቢስ ሰው ጀርባ ነው። ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ፤ የቂል አንደበት ግን ጥፋትን ይጋብዛል። የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ ድኽነት ግን የድኾች መጥፊያ ናት። የጻድቃን ደመወዝ ሕይወት ታስገኝላቸዋለች፤ የክፉዎች ትርፍ ግን ቅጣትን ታመጣባቸዋለች። ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል።
ምሳሌ 10:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነዚህ የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፤ ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሞኝ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል። አግባብ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ሀብት አይጠቅምም፤ ቀጥተኛነት ግን ከሞት ያድናል። እግዚአብሔር ደጋግ ሰዎችን እንዲራቡ አያደርግም፤ ክፉዎች ግን የተመኙትን እንዳያገኙ ያደርጋል። ስንፍና ያደኸያል፤ ተግቶ መሥራት ግን ያበለጽጋል፤ ብልኅ ሰው መከሩን በወቅቱ ይሰበስባል፤ በመከር ወራት የሚተኛ ግን ውርደት ይደርስበታል። ደግ ሰው በረከትን ያገኛል፤ ክፉ ሰው ግን ዐመፀኛነቱን በመልካም አነጋገር ይሸፍናል። የጻድቅ ሰው መታሰቢያ ለበረከት ይሆናል የክፉዎች ስም ግን ይጠፋል። በእውነት ጥበበኛ የሆነ ሰው ትእዝዞችን ይቀበላል፤ የሚለፈልፉ ሞኞች ግን ወደ ጥፋት ያመራሉ። በሁሉም ነገር ታማኝ ሰው ያለ ስጋት ይኖራል። የጠማማ ሰው እርምጃ ግን ይጋለጣል። በሰው ላይ መጠቃቀስ ችግርን ያመጣል፤ በግልጥ የሚነቅፍ ግን ሰላም እንዲገኝ ያደርጋል። የደግ ሰው ንግግር የሕይወት ምንጭ ነው፤ የክፉ ሰው ንግግር ግን የዐመፅ መሸፈኛ ነው። ጥላቻ ሁከትን ያነሣሣል፤ ፍቅር ግን በደልን ሁሉ አይታ በይቅርታ ታልፋለች። በአእምሮ የበሰሉ ሰዎች በማስተዋል ይናገራሉ። ሞኞች ግን ቅጣት መቀበል የሚገባቸው ናቸው። ጠቢባን በሚቻላቸው ዘዴ ሁሉ ዕውቀትን ያከማቻሉ፤ ሞኞች በሚናገሩበት ጊዜ ግን ጥፋት መምጣቱ አይቀርም። ባለጸጋን ሀብቱ እንደ ምሽግ ሆኖ ይጠብቀዋል፤ ድኻውን ግን ድኽነቱ ያጠፋዋል። የደግ ሰው መልካም ሥራ ሕይወትን ያስገኝለታል፤ የክፉ ሰው ኃጢአት ግን ቅጣትን ያስከትልበታል። ተግሣጽን የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ሕይወት መንገድ ያመራሉ፤ ከስሕተታቸው የማይማሩ ሰዎች ግን አደጋ ላይ ይወድቃሉ።
ምሳሌ 10:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሰሎሞን ምሳሌዎች። ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፥ አላዋቂ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው። በክፋት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፥ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል። ጌታ የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፥ የክፉዎችን ምኞት ግን ይገለብጣል። የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፥ የትጉ እጅ ግን ሀብታም ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፥ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል። በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፥ የክፉዎች አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፥ የክፉ ስም ግን ይጠፋል። በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፥ በከንፈሩ ሞኝ የሆነ ግን ይወድቃል። ያለ ነውር የሚመላለስ ተማምኖ ይሄዳል፥ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፥ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል። የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ማፍለቂያ ናት፥ የክፉዎች አፍ ግን ዐመፅን ይሸፍናል። ጥላቻ ክርክርን ታስነሣለች፥ ፍቅር ግን በደልን ሁሉ ትከድናለች። በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፥ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው። ጠቢባን እውቀትን ያከማቻሉ፥ የአላዋቂ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል። የሀብታም መዝገቡ የጸናች ከተማ ናት፥ የድሆች ውድቀት ድህነታቸው ነው። የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፥ የክፉ ገቢው ግን ለኃጢአት ነው። ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፥ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል።