ምሳሌ 1:1-7
ምሳሌ 1:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእስራኤል ንጉሥ፣ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ ጥበብንና ተግሣጽን ለመቀበል፤ ጥልቅ ሐሳብ የሚገልጡ ቃላትን ለማስተዋል፤ ጽድቅን፣ ፍትሕንና ሚዛናዊ ብያኔን በማድረግ፣ የተገራ ጠቢብ ልቦናን ለማግኘት፤ ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣ በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት፤ ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤ አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት፤ ይህም የጠቢባንን ምሳሌዎችና ተምሳሌቶች፣ አባባሎችና ዕንቈቅልሾች ይረዱ ዘንድ ነው። እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤ ተላሎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
ምሳሌ 1:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነዚህ ምሳሌዎች የዳዊት ልጅ የሆነው፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን የተናገራቸው ናቸው። ምሳሌዎቹም ጥበብንና መልካም ምክርን ለመገንዘብ፥ ጥልቅ አስተሳሰብ ያለውን የዕውቀት ቃል ለመረዳት የሚጠቅሙ ናቸው። እነርሱም እውነትን ፍትሕንና ቅንነትን በመከተል ሥርዓትንና ጥበብን ወደ ተሞላ ሕይወት ይመራሉ። በዕውቀት ላልበሰሉ ብልኅነትን ለወጣቶችም ዕውቀትንና ማስተዋልን እንዲያገኙ ያደርጋሉ። እነዚህ ምሳሌዎች ጠቢባን ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ፥ አስተዋዮችም ተጨማሪ መመሪያ የሚሆናቸውን ምክር እንዲያገኙ ያደርጋሉ። በዚህ ዐይነት ስውር የሆኑ የምሳሌዎችን ምሥጢር ጠቢባን የሚያቀርቡአቸውን እንቆቅልሾች መረዳት ያስችላሉ። እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ሞኞች ግን ጥበብና ሥነ ሥርዓትን ይንቃሉ።
ምሳሌ 1:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለእስራኤል የነገሠ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የጥበብንም ቃል ለማወቅ፥ የቃልን መልስ ለመቀበል በእውነት ጽድቅንም ለማወቅ ፍርድንም ለማቃናት፥ ብልሃትን ለየውሃን ይሰጥ ዘንድ ለሕፃናትና ለወጣቶችም አእምሮንና ዕውቀትን፥ ጠቢብ እነዚህን በመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይ ግን ምክርን ገንዘብ ያደርጋል። ምሳሌንና የተሸሸገውን ነገር፥ የጠቢባንን ቃልና ዕንቈቅልሾችን ያውቃል። የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ዕውቀት ለሚያደርጋት ሁሉ መልካም ናት። እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፥ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
ምሳሌ 1:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፥ ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፥ የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፥ ብልሃትን ለአላዋቂዎች ለመስጠት ለወጣቶችም እውቀትንና ጥንቃቄን፥ ጠቢብ እነዚህን በመስማት ዐዋቂነትን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። ምሳሌንና ምሥጢርን የጠቢባንን ቃልና ዕንቆቅልሸ ለማስተዋል። የዕውቀት መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ ሞኞች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።