ፊልጵስዩስ 1:12-30
ፊልጵስዩስ 1:12-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። ስለ ክርስቶስ ስም መታሰሬም በአደባባዩ ሁሉና በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቆአል። ከወንድሞቻችንም ብዙዎቹ በእስራቴ ምክንያት በጌታ ታመኑ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሀት ጨክነው ያስተምሩ ዘንድ እጅግ ተደፋፈሩ። ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ። በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምሁ ያውቃሉና። በኵራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አድርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሎአቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም። ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢሆን፥ በሐሰትም ቢሆን፥ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰውንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል። እኔም ይህቺ ሥራ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ወደ ሕይወት እንደምታደርሰኝ አውቃለሁ። በምንም እንደማላፍር ተስፋ እንደ አደረግሁና እንደታመንሁ እንደ ወትሮው በልብ ደስታ በግልጥነት፥ አሁንም የክርስቶስ ክብር በሕይወቴም ቢሆን፥ በሞቴም ቢሆን በሰውነቴ ይገለጣል። እኔ በሕይወት ብኖርም ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ብሞትም ዋጋ አለኝ። ነገር ግን በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆንም ምን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በከክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፤ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛል፤ ይበልጥብኛልም። ደግሞም ስለ እናንተ በሕይወተ ሥጋ ብኖር ይሻላል። ይህንም ዐውቄ ለማደጋችሁና በሃይማኖትም ለምታገኙት ደስታ እንደምኖር አምናለሁ። ዳግመኛ ወደ እናንተ በመምጣቴ በእኔ ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ የምታገኙት ክብር ይበዛላችሁ ዘንድ። ነገር ግን ምናልባት የመጣሁ እንደ ሆነ፥ ሳልኖርም ቢሆን በወንጌል ሃይማኖት እየተጋደላችሁ በአንድ መንፈስና በአንድ አካል ጸንታችሁ እንደምትኖሩ አይና እሰማ ዘንድ ሥራችሁ ለክርስቶስ ትምህርት እንደሚገባ ይሁን። የእነርሱ ጥፋት፥ የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ። ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቶአችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም። እንዲሁም እኔን እንዳያችሁኝ፥ የእኔንም ነገር እንደ ሰማችሁ ምንጊዜም ተጋደሉ።
ፊልጵስዩስ 1:12-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ መርዳቱን ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። ከዚህ የተነሣ እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደ ሆነ፣ በቤተ መንግሥት ዘበኞችና በሌሎችም ሁሉ ዘንድ ታውቋል። በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል። አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ። እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ ዐስበው፣ በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ። ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በቅንነትም ይሁን በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ እንደሚሆን ዐውቃለሁና። በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል። ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው። በሥጋ ከቈየሁ፣ ፍሬያማ ተግባር ይኖረኛል፤ ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ፣ ከክርስቶስም ጋር ልሆን እናፍቃለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና። ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ለእናንተ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ይህን በማስተዋል፣ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ፣ በሁላችሁ ዘንድ እንደምቈይና እንደምኖር ተረድቻለሁ። እንደ ገና መጥቼ በእናንተ ዘንድ በምሆንበት ጊዜ፣ በእኔ ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁ ደስታ ይበዛላችኋል። ብቻ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ፤ ይህ ከሆነ መጥቼ ባያችሁ ወይም በርቀት ሆኜ ስለ እናንተ ብሰማ፣ ለወንጌል እምነት እንደ አንድ ሰው ሆናችሁ በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ እንደምትቆሙ ዐውቃለሁ። በማንኛውም መንገድ በተቃዋሚዎቻችሁ አትሸበሩ፤ ይህ እነርሱ እንደሚጠፉ፣ እናንተ ግን እንደምትድኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምልክት ነው። በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቷችኋልና፤ ቀድሞ እንዳያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና።
ፊልጵስዩስ 1:12-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቍኦይ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።
ፊልጵስዩስ 1:12-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞቼ ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጉን እንድታውቁ እወዳለሁ። እኔም የታሰርኩት በክርስቶስ ምክንያት መሆኑን የቤተ መንግሥት ዘበኞችና ሌሎችም እዚያ ያሉት ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ። በእኔ መታሰር ምክንያት ከአማኞች ወንድሞች ብዙዎቹ በይበልጥ በጌታ የሚተማመኑ ሆነዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት ለማብሠር ከቀድሞ የበለጠ ድፍረት አግኝተዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የክርስቶስን የምሥራች ቃል የሚያበሥሩት በቅናት፥ ሌሎቹም በፉክክር መንፈስ ነው፤ ሌሎቹ ግን ክርስቶስን የሚሰብኩት በቅን ልቡና ነው። እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በቅን ልቡና የሚያበሥሩት ከፍቅር የተነሣ ነው፤ እነርሱም እኔ ለወንጌል ለመከላከል እዚህ የተጣልኩ መሆኔን ስለሚያውቁ ነው። እነዚያ ግን ስለ ክርስቶስ አጣምመው የሚሰብኩት በቅንነት ሳይሆን በራስ ወዳድነትና በእስራቴ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊያመጡብኝ አስበው ነው። ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው። በፍጹም እንደማላፍር በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን ዘወትር እንደማደርገውና ዛሬ በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። ስለዚህ ለእኔ ሕይወት ማለት በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው። ይሁን እንጂ በዚሁ ሥጋዊ አካሌ ቀጥዬ የምኖር ብሆን ፍሬ የሚሰጥ ሥራ መሥራት ማለት ነው፤ ሆኖም ግን ቀጥዬ ከመኖርና ከመሞት የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ተይዤአለሁ፤ በአንድ በኩል ከክርስቶስ ጋር መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ስለ ሆነ ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆንን እፈልጋለሁ ይኸውም ከክርስቶስ ጋር መኖር እጅግ የተሻለ ስለ ሆነ ነው። በሌላ በኩል በሕይወት መኖሬ ለእናንተ የበለጠ አስፈላጊ ነው። በዚህ በመተማመን እኔ ከሞት ተርፌ እምነታችሁ እንዲያድግና ደስታን እንድታገኙ ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ ዐውቃለሁ። እኔም እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ በእኔ ምክንያት ያላችሁ ትምክሕት በኢየሱስ ክርስቶስ ይበዛል። እንግዲህ ከሁሉም በላይ ሕይወታችሁ የክርስቶስን ወንጌል የሚያስመሰግን ይሁን፤ ይህም እኔ መጥቼ ባያችሁም ወይም ከእናንተ ብርቅ በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ መቆማችሁንና ወንጌልን በኅብረት ለማዳረስ መጋደላችሁን እሰማለሁ። ተቃዋሚዎቻችሁንም በምንም ነገር አትፍሩአቸው፤ ይህም ድፍረታችሁ ለእነርሱ የመጥፋታቸው ምልክት ሲሆን ለእናንተ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ የመዳኛችሁ ምልክት ነው። ክርስቶስን የማገልገል ዕድል የተሰጣችሁ በእርሱ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ምክንያት መከራ እንድትቀበሉም ጭምር ነው። ስለዚህ አሁን ከእኔ ጋር የመከራ ተካፋዮች ሆናችኋል፤ ይህም መከራ ከዚህ በፊት ደርሶብኝ ያያችሁትና አሁንም እየደረሰብኝ መሆኑን የምትሰሙት ነው።
ፊልጵስዩስ 1:12-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደሆነ በክብር ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፤ በጌታ ካሉት ወንድሞች የሚበዙት በእስራቴ ላይ ጽኑ መተማመን ኖሩዋቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ደፍረዋል። በእርግጥ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤ እነዚህ የኋለኞቹ ወንጌልን ለመመከት እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፤ እነዚያ የፊተኞቹ ግን በእስራቴ ላይ መከራን የሚያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ያለ ንጹሕ ልቦና ከራስ ወዳድነት በመነሣት ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ አማካይነት ለመዳኔ እንደሚሆንልኝ አውቄያለሁና፤ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በምንም ዓይነት ነገር አላፍርም፤ ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ እንደ ወትሮው እንዲሁ አሁንም በሥጋዬ ይከብራል ብዬ በሙሉ ድፍረት እናገራለሁ። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በሥጋ መኖር ማለት ለእኔ ፍሬያማ ሥራ የምሠራበት ቢሆን፥ ምን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህም በሁለቱ አማራጮች መካከል እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን ስለ እናንተ በሥጋ መኖሬ ይበልጥ አስፈላጊ ነገር ነው። ይህንንም ተረድቼ፥ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ከሁላችሁም ጋር እንደምቈይና እንደምኖር አውቃለሁ፤ በዚህም በእናንተ ዘንድ እንደገና ስለ መገኘቴ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ መመካታችሁ በእኔ እንዲበዛላችሁ ነው። ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ብቻ ኑሩ፤ በዚህም መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል እምነት አብራችሁ መጋደላችሁንና በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ መቆማችሁን እሰማለሁ። በምንም ዓይነት ነገር በተቃዋሚዎቻችሁ አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ስለ ሆነም በክርስቶስ የምታምኑ ብቻ ሳትሆኑ ስለ እርሱ መከራንም ደግሞ የምትቀበሉ ትሆናላችሁ፤ ይህም ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንደሆነ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።