ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። ስለ ክርስቶስ ስም መታሰሬም በአደባባዩ ሁሉና በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቆአል። ከወንድሞቻችንም ብዙዎቹ በእስራቴ ምክንያት በጌታ ታመኑ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሀት ጨክነው ያስተምሩ ዘንድ እጅግ ተደፋፈሩ። ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ። በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምሁ ያውቃሉና። በኵራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አድርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሎአቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም። ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢሆን፥ በሐሰትም ቢሆን፥ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰውንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል። እኔም ይህቺ ሥራ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ወደ ሕይወት እንደምታደርሰኝ አውቃለሁ። በምንም እንደማላፍር ተስፋ እንደ አደረግሁና እንደታመንሁ እንደ ወትሮው በልብ ደስታ በግልጥነት፥ አሁንም የክርስቶስ ክብር በሕይወቴም ቢሆን፥ በሞቴም ቢሆን በሰውነቴ ይገለጣል። እኔ በሕይወት ብኖርም ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ብሞትም ዋጋ አለኝ። ነገር ግን በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆንም ምን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በከክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፤ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛል፤ ይበልጥብኛልም። ደግሞም ስለ እናንተ በሕይወተ ሥጋ ብኖር ይሻላል። ይህንም ዐውቄ ለማደጋችሁና በሃይማኖትም ለምታገኙት ደስታ እንደምኖር አምናለሁ። ዳግመኛ ወደ እናንተ በመምጣቴ በእኔ ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ የምታገኙት ክብር ይበዛላችሁ ዘንድ። ነገር ግን ምናልባት የመጣሁ እንደ ሆነ፥ ሳልኖርም ቢሆን በወንጌል ሃይማኖት እየተጋደላችሁ በአንድ መንፈስና በአንድ አካል ጸንታችሁ እንደምትኖሩ አይና እሰማ ዘንድ ሥራችሁ ለክርስቶስ ትምህርት እንደሚገባ ይሁን። የእነርሱ ጥፋት፥ የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ። ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቶአችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም። እንዲሁም እኔን እንዳያችሁኝ፥ የእኔንም ነገር እንደ ሰማችሁ ምንጊዜም ተጋደሉ።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1:12-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos