የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ፊልጵስዩስ 1:1-15

ፊልጵስዩስ 1:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ባር​ያ​ዎች ከጳ​ው​ሎ​ስና ከጢ​ሞ​ቴ​ዎስ፥ በፊ​ል​ጵ​ስ​ዩስ ለሚ​ኖሩ፤ ከቀ​ሳ​ው​ስ​ትና ከዲ​ያ​ቆ​ናት ጋር በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ላሉ ቅዱ​ሳን ሁሉ፤ ከአ​ባ​ታ​ችን ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ ከጌ​ታ​ችን ከኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስም ሰላ​ምና ጸጋ ለእ​ና​ንተ ይሁን። እና​ን​ተን በማ​ስ​ብ​በት ጊዜ ሁሉ ዘወ​ትር አም​ላ​ኬን አመ​ሰ​ግ​ነ​ዋ​ለሁ። ስለ እና​ን​ተም ሁል​ጊዜ እጸ​ል​ያ​ለሁ፤ የደ​ስታ ጸሎ​ትም አደ​ር​ጋ​ለሁ። ከመ​ጀ​መ​ሪ​ያ​ዪቱ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ በወ​ን​ጌል ትም​ህ​ርት ከእኔ ጋር አንድ በመ​ሆ​ና​ችሁ፥ እርሱ የጀ​መ​ረ​ላ​ች​ሁን በጎ​ውን ሥራ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ እስ​ከ​ሚ​መ​ጣ​በት ቀን ድረስ እርሱ እን​ደ​ሚ​ፈ​ጽ​ም​ላ​ችሁ አም​ና​ለሁ። ስለ እና​ንተ ይህን ላስብ ይገ​ባ​ኛል፤ በም​ታ​ሰ​ር​በ​ትና በም​ከ​ራ​ከ​ር​በት፥ ወን​ጌ​ል​ንም በማ​ስ​ተ​ም​ር​በት ጊዜ ከእኔ ጋራ በጸጋ ስለ ተባ​በ​ራ​ችሁ በልቤ ውስጥ ናች​ሁና። በክ​ር​ስ​ቶስ ፍቅር ሁላ​ች​ሁን እን​ደ​ም​ወ​ዳ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምስ​ክሬ ነው። ስለ​ዚ​ህም በአ​እ​ም​ሮና በልብ ጥበብ ሁሉ ፍቅ​ራ​ችሁ እን​ዲ​በዛ፥ እን​ዲ​ጨ​ም​ርም እጸ​ል​ያ​ለሁ፤ የሚ​ሻ​ለ​ውን ሥራ እን​ድ​ት​መ​ረ​ም​ሩና እን​ድ​ት​ፈ​ትኑ፥ ክር​ስ​ቶስ በሚ​መ​ጣ​በት ቀን ያለ ዕን​ቅ​ፋት ቅዱ​ሳን ትሆኑ ዘንድ፦ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምስ​ጋ​ናና ክብ​ርም በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ የጽ​ድ​ቅን ፍሬ ትሞሉ ዘንድ እጸ​ል​ያ​ለሁ፤ ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ ይህ የደ​ረ​ሰ​ብኝ በእ​ው​ነት ወን​ጌ​ልን ለማ​ስ​ፋ​ፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወ​ድ​ዳ​ለሁ። ስለ ክር​ስ​ቶስ ስም መታ​ሰ​ሬም በአ​ደ​ባ​ባዩ ሁሉና በሰው ሁሉ ዘንድ ታው​ቆ​አል። ከወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ንም ብዙ​ዎቹ በእ​ስ​ራቴ ምክ​ን​ያት በጌታ ታመኑ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ቃል ያለ ፍር​ሀት ጨክ​ነው ያስ​ተ​ምሩ ዘንድ እጅግ ተደ​ፋ​ፈሩ። ከእ​ነ​ርሱ አን​ዳ​ን​ዶች በቅ​ና​ታ​ቸ​ውና በክ​ር​ክ​ራ​ቸው፥ ሌሎ​ችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክር​ስ​ቶስ ሊሰ​ብ​ኩና ሊያ​ስ​ተ​ምሩ የወ​ደዱ አሉ።

ፊልጵስዩስ 1:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋዮች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፤ ከቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በፊልጵስዩስ ላሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ቅዱሳን ለሆኑ ሁሉ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እናንተን ባስታወስሁ ቍጥር አምላኬን አመሰግናለሁ። ዘወትር ስለ ሁላችሁ ስጸልይ፣ በደስታ እጸልያለሁ፤ ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስካሁን ድረስ በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ሆናችኋልና። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ። በልቤ ስላላችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፤ በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋር የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ናችሁና። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያህል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ፍቅራችሁ በጥልቅ ዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ። ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው። አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ መርዳቱን ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። ከዚህ የተነሣ እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደ ሆነ፣ በቤተ መንግሥት ዘበኞችና በሌሎችም ሁሉ ዘንድ ታውቋል። በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል። አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ።

ፊልጵስዩስ 1:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፦ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤

ፊልጵስዩስ 1:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች ከሆኑት ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፥ በፊልጵስዩስ ከተማ ለሚኖሩ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ለሆኑ ሁሉ፥ እንዲሁም ለኤጲስ ቆጶሳትና ዲያቆናት፦ ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እናንተን በማስታውስበት ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ ስለ ሁላችሁም በምጸልይበት ጊዜ ሁሉ ጸሎቴ በደስታ የተሞላ ነው። ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስከ አሁን ወንጌልን በመስበክ የሥራዬ ተባባሪዎች ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ይህን መልካም ሥራ በእናንተ ሕይወት ውስጥ የጀመረ አምላክ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመለስበት ቀን ወደ ፍጻሜ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ ነኝ። አሁን በእስር ቤት ባለሁበት ጊዜና ከመታሰሬም በፊት ለወንጌል እውነት ለመከላከልና እርሱንም ለማጽናት እግዚአብሔር በጸጋው በሰጠኝ ዕድል ሁላችሁም ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ እናንተ ሁልጊዜ በልቤ ናችሁ። ስለዚህም ስለ እናንተ የሚሰማኝ ስሜት ትክክል ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ፍቅራችሁ ዕውቀትና ማስተዋል የሞላበት ሆኖ እያደገ እንዲሄድ እጸልያለሁ። ይኸውም የተሻለውን ነገር መርምራችሁ እንድታውቁና ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ቀን ንጹሖችና ነውር የሌለባችሁ ሆናችሁ እንድትገኙ ነው። በዚህም ዐይነት ሕይወታችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ የተሞላ ሆኖ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የምታስገኙ ትሆናላችሁ። ወንድሞቼ ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጉን እንድታውቁ እወዳለሁ። እኔም የታሰርኩት በክርስቶስ ምክንያት መሆኑን የቤተ መንግሥት ዘበኞችና ሌሎችም እዚያ ያሉት ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ። በእኔ መታሰር ምክንያት ከአማኞች ወንድሞች ብዙዎቹ በይበልጥ በጌታ የሚተማመኑ ሆነዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት ለማብሠር ከቀድሞ የበለጠ ድፍረት አግኝተዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የክርስቶስን የምሥራች ቃል የሚያበሥሩት በቅናት፥ ሌሎቹም በፉክክር መንፈስ ነው፤ ሌሎቹ ግን ክርስቶስን የሚሰብኩት በቅን ልቡና ነው።

ፊልጵስዩስ 1:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፥ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እናንተን ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግነዋለሁ፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ ሁላችሁም በደስታ እጸልያለሁ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ ነው። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንደሚፈጽመው በዚህ እርግጠኛ ሆኛለሁ፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ እጸልያለሁ፤ እንዲህም ያለው እውቀት የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ እንድትወድዱ ስለሚረዳችሁ ነው፤ በዚህም ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ንጹሖችና ያለ ነቀፋ በመሆን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝ የጽድቅ ፍሬ የተሞላችሁ እንድትሆኑ ነው። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደሆነ በክብር ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፤ በጌታ ካሉት ወንድሞች የሚበዙት በእስራቴ ላይ ጽኑ መተማመን ኖሩዋቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ደፍረዋል። በእርግጥ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤