የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ፊልጵስዩስ 1:1-15

ፊልጵስዩስ 1:1-15 NASV

የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋዮች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፤ ከቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በፊልጵስዩስ ላሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ቅዱሳን ለሆኑ ሁሉ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እናንተን ባስታወስሁ ቍጥር አምላኬን አመሰግናለሁ። ዘወትር ስለ ሁላችሁ ስጸልይ፣ በደስታ እጸልያለሁ፤ ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስካሁን ድረስ በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ሆናችኋልና። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ። በልቤ ስላላችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፤ በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋር የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ናችሁና። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያህል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ፍቅራችሁ በጥልቅ ዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ። ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው። አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ መርዳቱን ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። ከዚህ የተነሣ እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደ ሆነ፣ በቤተ መንግሥት ዘበኞችና በሌሎችም ሁሉ ዘንድ ታውቋል። በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል። አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ።