ዘኍልቍ 6:1-21

ዘኍልቍ 6:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን እን​ዲህ ብሎ ተና​ገ​ረው፦ “ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች እን​ዲህ ብለህ ንገ​ራ​ቸው፤ ወንድ ወይም ሴት ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ራሱን የተ​ለየ ያደ​ርግ ዘንድ ልዩ ስእ​ለት ቢሳል፥ ከወ​ይን ጠጅና ከሚ​ያ​ሰ​ክር መጠጥ ራሱን የተ​ለየ ያድ​ርግ፤ ከወ​ይን ወይም ከሌላ ከሚ​ያ​ሰ​ክር ነገር የሚ​ገ​ኘ​ውን ሆም​ጣጤ አይ​ጠጣ፤ የወ​ይ​ንም ጭማቂ አይ​ጠጣ፤ የወ​ይ​ንም እሸት ወይም ዘቢብ አይ​ብላ። ራሱን የተ​ለየ ባደ​ረ​ገ​በት ወራት ሁሉ ከወ​ይን የሆ​ነ​ውን ነገር ሁሉ ከው​ስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ደረ​ቀው ዘቢብ ድረስ አይ​ብላ። “ራሱን ለመ​ለ​የት ስእ​ለት ባደ​ረ​ገ​በት ወራት ሁሉ ራሱን አይ​ላጭ፤ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ለ​የ​በት ወራት እስ​ኪ​ፈ​ጸም ድረስ ቅዱስ ይሆ​ናል፤ የራ​ሱ​ንም ጠጕር ያሳ​ድ​ጋል። “ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ራሱን የተ​ለየ ባደ​ረ​ገ​በት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይ​ቅ​ረብ። ለአ​ም​ላኩ ያደ​ረ​ገው ብፅ​ዐት በራሱ ላይ ነውና አባቱ፥ ወይም እናቱ፥ ወይም ወን​ድሙ፥ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰው​ነ​ቱን አያ​ር​ክ​ስ​ባ​ቸው። በብ​ፅ​ዐቱ ወራት ሁሉ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ቀ​ደሰ ነውና። “ሰውም በአ​ጠ​ገቡ ድን​ገት ቢሞት የራሱ ብፅ​ዐት ይረ​ክ​ሳል፤ እርሱ በሚ​ነ​ጻ​በት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰ​ባ​ተ​ኛው ቀን ይላ​ጨው። በስ​ም​ን​ተ​ኛ​ውም ቀን ሁለት ዋኖ​ሶች ወይም ሁለት የር​ግብ ግል​ገ​ሎች ወደ ምስ​ክሩ ድን​ኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህ​ኑም አን​ዲ​ቱን ለኀ​ጢ​አት መሥ​ዋ​ዕት ሁለ​ተ​ኛ​ዪ​ቱ​ንም ለሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ያቀ​ር​ባል፤ በሬ​ሳም የተ​ነሣ ኀጢ​አት ሠር​ቶ​አ​ልና ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል፤ በዚ​ያም ቀን ራሱን ይቀ​ድ​ሰ​ዋል። በስ​እ​ለቱ ወራ​ትም ሁሉ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይቀ​ደ​ሳል፤ የአ​ንድ ዓመ​ትም ተባት ጠቦት ለበ​ደል መሥ​ዋ​ዕት ያምጣ፤ ስእ​ለቱ ግን ረክ​ሶ​አ​ልና ያለ​ፈው ወራት ሁሉ አይ​ቈ​ጠ​ር​ለ​ትም። “የተ​ሳ​ለው ሰው ሕግ ይህ ነው፤ የስ​እ​ለቱ ወራት በተ​ፈ​ጸመ ጊዜ ራሱ ወደ ምስ​ክሩ ድን​ኳን ደጃፍ ይቅ​ረብ፤ ቍር​ባ​ኑ​ንም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያቅ​ርብ። ነውር የሌ​ለ​በት የአ​ንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት፥ ነው​ርም የሌ​ለ​ባ​ትን የአ​ንድ ዓመት እን​ስት ጠቦት ለኀ​ጢ​አት መሥ​ዋ​ዕት፥ ነውር የሌ​ለ​በ​ትን አውራ በግ ለደ​ኅ​ን​ነት መሥ​ዋ​ዕት፥ አንድ ሌማ​ትም በዘ​ይት የተ​ለ​ወሰ የስ​ንዴ ቂጣ እን​ጀራ፥ በዘ​ይ​ትም የተ​ቀባ ስስ ቂጣ፥ የእ​ህ​ሉ​ንም ቍር​ባን፥ የመ​ጠ​ጡ​ንም ቍር​ባን ያቅ​ርብ። ካህ​ኑም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያቅ​ር​በው። የኀ​ጢ​አ​ቱ​ንም መሥ​ዋ​ዕት የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ው​ንም መሥ​ዋ​ዕት ያሳ​ር​ግ​ለ​ታል። አው​ራ​ው​ንም በግ ለደ​ኅ​ን​ነት መሥ​ዋ​ዕት ከሌ​ማቱ ቂጣ እን​ጀራ ጋር ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያቀ​ር​ባል፤ ካህ​ኑም ደግሞ የእ​ህ​ሉን ቍር​ባ​ንና የመ​ጠ​ጡን ቍር​ባን ያቀ​ር​ባል። የተ​ሳ​ለ​ውም የተ​ሳ​ለ​ውን የራስ ጠጕር በም​ስ​ክሩ ድን​ኳን አጠ​ገብ ይላ​ጫል፤ የስ​እ​ለ​ቱ​ንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደ​ኅ​ን​ነት መሥ​ዋ​ዕት በታች ወዳ​ለው እሳት ይጥ​ለ​ዋል። ካህ​ኑም የተ​ቀ​ቀ​ለ​ውን የአ​ው​ራ​ውን በግ ወርች፥ ከሌ​ማ​ቱም አንድ ቂጣ እን​ጎቻ፥ አን​ድም ስስ ቂጣ ይወ​ስ​ዳል፤ የተ​ሳ​ለ​ው​ንም የራስ ጠጕር ከተ​ላጨ በኋላ በባ​ለ​ስ​እ​ለቱ እጆች ላይ ያኖ​ራ​ቸ​ዋል። ካህ​ኑም እነ​ዚ​ህን ሁሉ ቍር​ባን አድ​ርጎ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያቀ​ር​ባል፤ ይህም የቍ​ር​ባን ፍር​ም​ባና የመ​ባው ወርች ለካ​ህኑ የተ​ቀ​ደሰ ነው፤ ከዚ​ያም በኋላ ባለ​ስ​እ​ለቱ ወይን ይጠ​ጣል። “ስእ​ለ​ቱን የተ​ሳ​ለው የባ​ለ​ስ​እ​ለቱ፥ እጁም ከሚ​ያ​ገ​ኘው ሌላ ስለ ስእ​ለቱ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሚ​ያ​ቀ​ር​በው የቍ​ር​ባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእ​ለ​ቱን እንደ ተሳለ እንደ ስእ​ለቱ ሕግ እን​ዲሁ ያደ​ር​ጋል።”

ዘኍልቍ 6:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ ‘ወንድም ሆነ ሴት ናዝራዊ ይሆን ዘንድ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመለየት ስእለት ቢሳል፣ ከወይን ጠጅና ከሌላም ከሚያሰክር መጠጥ ይታቀብ፤ የወይንም ሆነ የሚያሰክር የሌላ መጠጥ ሖምጣጤ አይጠጣ፤ እንዲሁም የወይን ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ። በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ተክል የሚገኘውን ማንኛውም ነገር፣ የወይኑን ዘር፣ ግልፋፊውንም እንኳ ቢሆን አይብላ። “ ‘ስእለት ተስሎ ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ምላጭ ራሱን አይንካው፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የተቀደሰ ይሁን፤ የራስ ጠጕሩንም ያሳድግ። ራሱን ለእግዚአብሔር በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። ራሱን ለእግዚአብሔር የለየበት ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱም ይሁን እናቱ፣ ወንድሙም ይሁን እኅቱ ቢሞቱ ለእነርሱ ሲል እንኳ ራሱን አያርክስ። ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። “ ‘ድንገት ሰው አጠገቡ ሞቶ ለእግዚአብሔር የተለየበትን ጠጕሩን ቢያረክስበት፣ በሚነጻበት ዕለት ማለት በሰባተኛው ቀን ጠጕሩን ይላጭ። በስምንተኛው ቀን ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ዘንድ ያምጣ። ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት ሌላውን ማስተስረያ እንዲሆንለት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው፤ በሬሳ አጠገብ በመገኘቱ ኀጢአት ሠርቷልና። በዚያ ዕለት ጠጕሩን ይቀድስ። ራሱን የተለየ ያደረገበትን ጊዜ ለእግዚአብሔር መቀደስ አለበት፤ እንዲሁም የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ። ያለፉት ቀኖች አይቈጠሩም፤ በተለየበት ጊዜ ረክሷልና። “ ‘እንግዲህ ናዝራዊ የመለየቱ ጊዜ ሲያበቃ ሥርዐቱ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ እንዲመጣ ይደረጋል። እዚያም መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ይኸውም፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኀጢአት መሥዋዕት እንዲሁም እንከን የሌለበት አውራ በግ ለኅብረት መሥዋዕት ሲሆን፣ ከእነዚህም ጋራ የሚቀርበውን የእህልና የመጠጥ ቍርባን ቂጣ ማለት ከላመ ዱቄት በዘይት የተለወሱ ዕንጐቻዎች እንዲሁም በሥሡ የተጋገረና ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ያምጣ። “ ‘ካህኑ እነዚህን የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል። በመሶብ ያለውን ቂጣ፣ እንዲሁም አውራ በጉን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ ካህኑ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። “ ‘ከዚያም ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጨው፤ ጠጕሩንም ወስዶ ከኅብረቱ መሥዋዕት ሥር በሚነድደው እሳት ውስጥ ይጨምረው። “ ‘ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጕር ከተላጨ በኋላ፣ ካህኑ የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች እንዲሁም ከመሶቡ ላይ እርሾ የሌለበትን አንድ ወፍራምና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ ናዝራዊው ያስይዘው ከዚያም ካህኑ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም የተቀደሱ ናቸው። ከተወዘወዘው ፍርምባና ከቀረበው ወርች ጋራ የተቀደሱ የካህኑ ድርሻ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል። “ ‘ስእለቱን ለመፈጸም ለእግዚአብሔር ለሚሳል ናዝራዊ ሕጉ ይኸው ነው፤ ሊቀርብ ከሚችለው በላይ ለእግዚአብሔር ለመስጠት ቃል ለሚገባው ነገር እንደ ናዝራዊነቱ በተሳለው መሠረት መሆን አለበት። በናዝራዊነት ሕግ መሠረት የተሳለውን ስእለት መፈጸም ይገባዋል።’ ”

ዘኍልቍ 6:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፦ ሰው ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል፥ ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ። ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ። ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይደርስም፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጕር ያሳድጋል። ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። ለአምላኩ ያደረገው ስእለት በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰውነቱን አያርክስባቸው። ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት የተለየውንም ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨው። በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል። ራሱን የተለየ ያደረገበትን ወራትም ለእግዚአብሔር ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል። የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤ ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለደኅንነት መሥዋዕት፥ አንድ ሌማትም ቂጣ እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን ያቅርብ። ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል። አውራውንም በግ ለደኅንነት መሥዋዕት ከሌማቱ ቂጣ እንጀራ ጋር ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን ያቀርባል። ናዝራዊውም የተለየውን የራሱን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ይላጫል፥ የመለየቱንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደኅንነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል። ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም አንድ ቂጣ እንጐቻ አንድም ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተለየውንም የራስ ጠጕር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤ ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚነሣው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ይጠጣ ዘንድ ይችላል። ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ እጁም ከሚያገኘው ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የቍርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል።

ዘኍልቍ 6:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገር፦ ወንድ ወይም ሴት ማንኛውም ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር በመለየት ናዝራዊ ለመሆን ስእለት ቢያደርግ፥ የወይን ጠጅም ሆነ ማናቸውንም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የተሠራ ሆምጣጤ ወይም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ፤ በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ሐረግ የሚገኘውን ሁሉ የወይኑን ፍሬ ግልፋፊ ወይም ዘር አይብላ። “ስእለት ተስሎ በናዝራዊነት እስካለ ድረስ ራሱን ምላጭ አይንካው፤ የናዝራዊነት ጊዜው እስኪፈጸም ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ (የተቀደሰ) ይሆናል፤ የራሱንም ጠጒር ያሳድጋል። በናዝራዊነት በአለበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሞተ ሰው በድን አይቅረብ፤ ለአምላኩ ያቀረበው የናዝራዊነት ስእለት በራሱ ላይ ስለ ሆነ አባቱ ወይም እናቱ፥ ወንድሙ ወይም እኅቱ ቢሞቱ አስከሬናቸውን በመንካት ራሱን አያርክስ። ናዝራዊ እስከ ሆነ ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ (የተቀደሰ) ነው። “በድንገት አንድ ሰው በአጠገቡ ቢሞት፥ የተቀደሰውን ራሱንም ቢያረክስ፥ በሰባተኛው ቀን ራሱን ይላጭ። በስምንተኛው ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት ርግቦች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደሚገኘው ካህን ያምጣ። ካህኑም አንዱን ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት፥ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ናዝራዊው ሬሳ በመንካቱ ስለ ረከሰ ያስተሰርይለታል፤ በዚያኑ ቀን ናዝራዊው ጠጒሩን እንደገና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ያደርገዋል። በናዝራዊነትም ለማገልገል ራሱን እንደገና ለእግዚአብሔር የተለየ ያደርጋል፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰው ጠጒሩ ከመርከሱ የተነሣ ከዚያ በፊት በናዝራዊነት የነበረበት ክፍለ ጊዜ አይቈጠርለትም፤ ስለ በደልም ለሚከፈለው ዋጋ አንድ ዓመት የሞላው የበግ ጠቦት ያምጣ። “አንድ ናዝራዊ የናዝራዊነት ስእለቱን ሲጨርስ የሚፈጽመው ሕግ ይህ ነው፦ ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ በር ሄዶ፥ እዚያ ቊርባኑን ለእግዚአብሔር ያቀርባል፤ ይኸውም ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ዓመት የሞላው የበግ ጠቦት፥ ስለ ኃጢአት ስርየት ለሚቀርበውም መሥዋዕት አንድ ዓመት የሞላት አንዲት የበግ ቄብ እንዲሁም የአንድነት መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ያቀርባል ማለት ነው። ደግሞም እርሾ ሳይነካው የተጋገረ አንድ መሶብ እንጀራ፥ በወይራ ዘይት ከተለወሰ ዱቄት የተጋገረ ውፍረት ያለው ኅብስት፥ በወይራ ዘይት የተቀቡ ስስ ቂጣዎች ጭምር ከሚቀርበው ከእህል ቊርባንና ከመጠጥ መባ ጋር አብሮ ይቅረብ። “ካህኑም ይህን ሁሉ የኃጢአት ስርየትና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባቸዋል። አውራውን በግ የአንድነት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀርበዋል፤ እርሱንም በመሶብ ካለው እንጀራ ጋር ያቀርበዋል፤ ቀጥሎም የእህሉን ቊርባንና የመጠጡን መባ ያቀርባል። በመገናኛው ድንኳን በር መግቢያ ላይ ናዝራዊው ጠጒሩን ላጭቶ የአንድነት መሥዋዕት በሚቃጠልበት እሳት ላይ ያኖረዋል። “ናዝራዊው የተቀደሰውን ጠጒሩን ከተላጨ በኋላ ካህኑ የተቀቀለውን አውራ በግ ወርች፥ በመሶብ ውስጥ ካለው አንድ ኅብስትና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ ናዝራዊ በሆነው ሰው እጆች ላይ ያኖረዋል፤ ከዚህም በኋላ ካህኑ ይህን ሁሉ ወስዶ ለእግዚአብሔር የሚወዘወዝ ልዩ መባ አድርጎ ያቀርበዋል፤ ይህም ሁሉ የካህኑ ድርሻ ሆኖ ከሚነሣው ከአውራው በግ ፍርንባና ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ድርሻ ይሆናል፤ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት የሚፈቀድለትም ከዚያን በኋላ ነው። “እንግዲህ እነዚህ ስለ ናዝራውያን የተሰጡ የሕግ መመሪያዎች ናቸው፤ ነገር ግን አንድ ናዝራዊ በስእለቱ መሠረት ሊያቀርብ ከሚገባው በላይ ለመስጠት ቃል ቢገባ በገባው ቃል መሠረት ስእለቱን መፈጸም አለበት።”

ዘኍልቍ 6:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወንድ ወይም ሴት ራሳቸውን ለጌታ ለመለየት የናዝራዊነት ስእለት ቢሳሉ፥ ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን ይለይ፤ ከወይን ወይም ከሚያሰክር መጠጥ የሚሠራን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ ማንኛውንም ዓይነት የወይን ዘለላ ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ዘለላ ወይም ዘቢብ አይብላ። ራሱን በለየበት ወራት ሁሉ ከወይን ጠጅ የሚሠራውን ሌላ ነገር ሁሉ እንዲሁም የውስጡን ፍሬ ወይም ግልፋፊውን እንኳ አይብላ። “ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ለጌታ የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጉር ያሳድግ። “ለጌታ ራሱን በለየበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። ለአምላኩ ያደረገው ቅድስና በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ራሱን ስለ እነርሱ አያርክስ። ራሱን በለየበት ወራት ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ነው። “ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት እርሱም የተቀደሰውን ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጫል፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨዋል። በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል። ራሱን የለየበትን ወራትም ለጌታ ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያመጣል፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል። “የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤ ቁርባኑንም ለጌታ ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለአንድነት መሥዋዕት፥ አንድ ሌማትም እርሾ ያልገባበት እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ እርሾ ያልገባበት ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቁርባን፥ የመጠጡንም ቁርባን ያቅርብ። ካህኑም በጌታ ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል። አውራውንም በግ ለአንድነት መሥዋዕት ከሌማቱ እርሾ ካልገባበት እንጀራ ጋር ወደ ጌታ ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቁርባንና የመጠጡን ቁርባን ያቀርባል። ናዝራዊውም የተቀደሰውን የራሱን ጠጉር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጫል፥ የተቀደሰውንም ራስ ጠጉር ወስዶ ከአንድነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል። ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም እርሾ ያልገባበትን አንድ የቂጣ እንጐቻ እርሾም ያልገባበትን አንድ ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተቀደሰውንም የራስ ጠጉር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤ ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚቀርበው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ድርሻው ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ሊጠጣ ይችላል። “ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ የመግዛት አቅሙ ከሚፈቅድለት ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለጌታ የሚያቀርበው የቁርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል።”