የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍል 28:1-10

ዘኍል 28:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን እን​ዲህ ብሎ ተና​ገ​ረው፦ “የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች እን​ዲህ ብለህ እዘ​ዛ​ቸው፦ ቍር​ባ​ኔን፥ መባ​ዬ​ንና የበጎ መዓዛ መሥ​ዋ​ዕ​ቴን በበ​ዓ​ላት ቀኖች ታቀ​ር​ቡ​ልኝ ዘንድ ጠብቁ። እን​ዲ​ህም በላ​ቸው፦ በእ​ሳት ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የም​ታ​ቀ​ር​ቡት ቍር​ባን ይህ ነው፤ ለሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ነውር የሌ​ለ​ባ​ቸ​ውን ሁለት የአ​ንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦ​ቶች ዕለት ዕለት ታቀ​ር​ባ​ላ​ችሁ። አን​ዱን ጠቦት በማ​ለዳ፥ ሌላ​ው​ንም ጠቦት በማታ አቅ​ርቡ፤ ለእ​ህ​ልም ቍር​ባን የኢን መስ​ፈ​ሪያ አራ​ተኛ እጅ በሆነ፥ ተወ​ቅጦ በተ​ጠ​ለለ ዘይት የተ​ለ​ወሰ የኢፍ መስ​ፈ​ሪያ ዐሥ​ረኛ እጅ መል​ካም ዱቄት ታቀ​ር​ባ​ላ​ችሁ። በእ​ሳት ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጎ መዓዛ እን​ዲ​ሆን የቀ​ረበ፥ በሲና ተራራ የተ​ሠራ ለዘ​ወ​ትር የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ነው። የመ​ጠ​ጡም ቍር​ባን ለአ​ንድ ጠቦት የኢን መስ​ፈ​ሪያ አራ​ተ​ኛው እጅ ነው፤ በመ​ቅ​ደሱ ውስጥ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለመ​ጠጥ ቍር​ባን መጠጥ ታፈ​ስ​ሳ​ላ​ችሁ። ሌላ​ው​ንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀ​ር​ባ​ላ​ችሁ፤ የእ​ህ​ሉን ቍር​ባ​ንና የመ​ጠ​ጡን ቍር​ባን በማ​ለዳ እን​ዳ​ቀ​ረ​ባ​ችሁ በእ​ሳት ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጎ መዓዛ እን​ዲ​ሆን ታቀ​ር​ቡ​ታ​ላ​ችሁ። “በሰ​ን​በ​ትም ቀን ነውር የሌ​ለ​ባ​ቸ​ውን ሁለት የአ​ንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦ​ቶች፥ ለእ​ህ​ልም ቍር​ባን በዘ​ይት የተ​ለ​ወሰ ከመ​ስ​ፈ​ሪ​ያው ከዐ​ሥር እጅ ሁለት እጅ መል​ካም ዱቄት፥ የመ​ጠ​ጡ​ንም ቍር​ባን ታቀ​ር​ባ​ላ​ችሁ። በዘ​ወ​ትር ከሚ​ቃ​ጠ​ለው መሥ​ዋ​ዕት ሌላ፥ ከመ​ጠ​ጡም ቍር​ባን ሌላ፥ በየ​ሰ​ን​በቱ ሁሉ የም​ታ​ቀ​ር​ቡት የሚ​ቃ​ጠ​ለው መሥ​ዋ​ዕት ይህ ነው።

ዘኍል 28:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህን ትእዛዝ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ስጣቸው፤ ‘ሽታው ደስ እንዲያሰኘኝ በእሳት የሚቀርብልኝን የምግብ ቍርባን የተወሰነውን ጊዜ ጠብቃችሁ አቅርቡልኝ።’ ደግሞም እንዲህ በላቸው፤ ‘በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምታቀርቡት መሥዋዕት ይህ ነው፤ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በየዕለቱ አቅርቡ። አንዱን ጠቦት ጧት ሌላውን ደግሞ ማታ አቅርቡ፤ ከዚህም ጋር ተወቅጦ በተጠለለ በሂን አንድ አራተኛ የወይራ ዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አዘጋጁ። ይህም ሽታው ደስ እንዲያሰኝ በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ ምሥዋዕት ሲሆን፣ በሲና ተራራ የተደነገገ መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋር አብሮት የሚቀርበውም የመጠጥ ቍርባን ፈልቶ የወጣለት የሂን አንድ አራተኛ መጠጥ ይሆናል፤ የመጠጡንም ቍርባን በተቀደሰው ቦታ ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አፍስሱት። ሁለተኛውንም ጠቦት ጧት ባቀረባችሁት ዐይነት አድርጋችሁ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር ማታ አቅርቡት፤ ይህም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። “ ‘በሰንበት ዕለት፣ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የማይገኝባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መሥዋዕት ከመጠጥ ቍርባኑና በዘይት ከተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ጋር አቅርቡ። ይህም ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ በየሰንበቱ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

ዘኍል 28:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ መብሌን፥ ለእኔ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የተደረገውን ቍርባኔን፥ መባዬን በየጊዜው ታቀርቡልኝ ዘንድ ጠብቁ። እንዲህም በላቸው፦ በእሳት ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፤ ለዘወትር ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ዕለት ዕለት ታቀርባላችሁ። አንዱን ጠቦት በማለዳ፥ ሌላውንም ጠቦት በማታ አቅርብ፤ ለእህልም ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት ታቀርባለህ። በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የቀረበ በሲና ተራራ የተሠራ ለዘወትር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። የመጠጡ ቍርባን ለአንድ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛው እጅ ነው፤ በመቅደሱ ውስጥ ለእግዚአብሔር ለመጠጥ ቍርባን መጠጥ ታፈስሳለህ። ሌላውንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀርባለህ፤ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን በማለዳ እንዳቀረብህ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ታቀርበዋለህ። በሰንበትም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህልም ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ የመጠጡንም ቍርባን ታቀርባላችሁ። በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ በየሰንበቱ ሁሉ የምታቀርቡት የሚቃጠለው መሥዋዕት ይህ ነው።

ዘኍል 28:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤል ሕዝብ የምትሰጣቸው ትእዛዝ ይህ ነው፦ መዓዛው ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቃጠል የምግብ ቊርባን እንዲያቀርቡልኝ ንገራቸው።” “ለእኔ የሚቀርበውም በእሳት የሚቃጠል የምግብ ቊርባን የሚከተለው ነው፦ በየቀኑ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ዓመት የሞላቸውና ምንም ነውር የሌለባቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች ይሁኑ፤ የመጀመሪያው ጠቦት ጠዋት፥ ሁለተኛውም ጠቦት ማታ እንዲቀርብ አድርጉ፤ ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር ምርጥ በሆነ፥ በአንድ ሊትር የወይራ ዘይት የተለወሰ፥ አንድ ኪሎ ዱቄት የእህል ቊርባን ሆኖ ይቅረብ፤ ይህም በፍጹም የሚቃጠለው የዘወትር መሥዋዕት ነው፤ የዚህ ዐይነቱ መሥዋዕት መዓዛው እኔን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ሆኖ በመጀመሪያ የቀረበው በሲና ተራራ ላይ ነበር። ከመጀመሪያው ጠቦት ጋር የመጠጥ መባ ሆኖ እንዲቀርብ አንድ ሊትር ጠንካራ መጠጥ በመሠዊያው ላይ አፍስሱበት። ሲመሽም ሁለተኛውን ጠቦት ልክ የመጀመሪያው በቀረበበት ሁኔታ የመጠጡንም መባ ጨምራችሁ አቅርቡ፤ እርሱም መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ይሆናል። “በሰንበት ቀን አንድ ዓመት የሞላቸውና ምንም ነውር የሌለባቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ በወይራ ዘይት የተለወሰ ሁለት ኪሎ ምርጥ ዱቄት ለእህል ቊርባን አቅርቡ፤ እንዲሁም የመጠጡንም መባ አቅርቡ፤ ከመጠጡ መባና ከሚቀርበው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በየሰንበቱ ይቅረብ።

ዘኍል 28:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ “‘ማዕዴን፥ ለእኔ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን ቁርባኔን፥ መባዬን በተገቢው ጊዜ እንድታቀርቡልኝ በጥንቃቄ ልብ በሉ።’ እንዲህም በላቸው፦ ‘ለጌታ በእሳት የምታቀርቡት ቁርባን ይህ ነው፤ ለዘወትር ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ዕለት ዕለት ታቀርባላችሁ። አንዱን ጠቦት በማለዳ፥ ሌላውንም ጠቦት በማታ አቅርብ፤ የኢንም መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቁርባን ታቀርባለህ። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በሲና ተራራ ላይ ተሰናድቶ በእሳት የቀረበ የዘወትር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። የመጠጡ ቁርባን ለአንድ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛው እጅ ይሁን፤ በመቅደሱ ውስጥ ለጌታ ለመጠጥ ቁርባን መጠጥ አፍስስ። ሌላውንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀርባለህ፤ የእህሉን ቁርባንና የመጠጡን ቁርባን በማለዳ እንዳቀረብህ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ።’ “በሰንበትም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህልም ቁርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ የመጠጡንም ቁርባን ታቀርባላችሁ። ዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ፥ ከመጠጡም ቁርባን ሌላ፥ በየሰንበቱ ሁሉ የምታቀርቡት የሚቃጠለው መሥዋዕት ይህ ነው።