ዘኍል 27:12-23
ዘኍል 27:12-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደዚህ በናባው አሻገር ወዳለው ተራራ ውጣ፤ ለእስራኤልም ልጆች ይገዙአት ዘንድ እኔ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እያት፤ ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ እንደ ተጨመረ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትጨመራለህ። እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አላከበራችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የክርክር ውኃ ነው።” ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የሥጋና የነፍስ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የሚሆነውን ሰው ይሹም፤ በፊታቸው የሚወጣውንና የሚገባውን፥ የሚያስወጣቸውንና፥ የሚያስገባቸውንም፥ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን።” እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “መንፈስ ቅዱስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ በካህኑም በአልዓዛር ፊት አቁመው፤ በማኅበሩም ፊት እዘዘው፤ ስለ እርሱም በፊታቸው እዘዝ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ ስጠው። በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፤ በቃሉም ይግቡ።” ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንደ አዘዘው፥ እጁን በላዩ ጫነበትና፥ ሾመው፤ አዘዘውም።
ዘኍል 27:12-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በዓባሪም ሸንተረር ላይ ወዳለው ወደዚህ ተራራ ውጣና ለእስራኤላውያን የሰጠኋቸውን ምድር እይ። ካየኸውም በኋላ አንተም እንደ ወንድምህ እንደ አሮን ወደ ሕዝብህ ትሰበሰባለህ፤ ምክንያቱም ማኅብረ ሰቡ በጺን ምድረ በዳ ባለው ውሃ አጠገብ ባመፁ ጊዜ እኔን በሕዝቡ ፊት ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ሁለታችሁም ትእዛዜን ስላልጠበቃችሁ ነው።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ የመሪባ ውሃ ነው። ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መንፈስ አምላክ (ኤሎሂም) የሆነ ጌታ እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ ማኅበረ ሰብ ላይ ሰው ይሹም፤ እርሱም፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን በፊቱ የሚወጣና የሚገባ፣ መርቶ የሚያወጣውና የሚያገባው እንዲሆን ነው።” ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት። በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አድርገው፤ በፊታቸውም ሹመው፤ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ እንዲታዘዝለትም ከሥልጣንህ ከፍለህ ስጠው። እርሱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሆኖ በኡሪም በመጠየቅ ውሳኔ በሚያስገኝለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል፤ እርሱም ሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በአልዓዛር ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በእርሱም ቃል ይገባሉ።” ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው የእስራኤል ማኅበር ፊት አቆመው፤ ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት እጁን በራሱ ላይ ጭኖ ሾመው።
ዘኍል 27:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤ ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ። እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው። ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በፊታቸው የሚወጣውን በፊታቸውም የሚገባውን የሚያስወጣቸውንም የሚያስገባቸውንም ሰው የሥጋ ሁሉ መንፈስ አምላክ እግዚአብሔር በማኅበሩ ላይ ይሹመው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት። በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ። ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ እግዚአብሔርም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በላዩ ጫነበት፥ አዘዘውም።
ዘኍል 27:12-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ዐባሪም ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ልሰጣቸው ያቀድኩትን ምድር ሁሉ እይ፤ እርሱንም ካየህ በኋላ ወንድምህ አሮን እንደ ሞተ አንተም ትሞታለህ፤ ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ በትእዛዜ ላይ ዐምፃችሁ ነበር፤ መላው ማኅበር በመሪባ ውሃ ዘንድ ሳሉ በእኔ ላይ በዐመፁ ጊዜ የተቀደሰውን ኀይሌን በእነርሱ ፊት መግለጥ እምቢ ብላችኋል፤” (መሪባ በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ ምንጭ ነው።) ሙሴም ወደ ጌታ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ለሰው ሁሉ ሕይወትን የምትሰጥ፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ሕዝብህ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን፥ ሕዝብህን የሚመራ አንድ ሰው ምረጥ።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በመንፈስ ጠንካራ የሆነውን የነዌን ልጅ ኢያሱን ውሰድና እጆችህን በራሱ ላይ ጫን፤ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አድርገው፤ በእነርሱም ሁሉ ፊት የአንተ ተተኪ መሆኑን አስታውቅ። መላው የእስራኤል ማኅበር እርሱን ይታዘዙት ዘንድ የሥልጣንህ ተካፋይ አድርገው። ካህኑ አልዓዛር በኡሪም አማካይነት ፈቃዴን የሚያውቅ ስለ ሆነ ኢያሱ በአልዓዛር ይደገፋል፤ በዚህም ዐይነት አልዓዛር ኢያሱንና መላውን የእስራኤል ማኅበር በተግባር አፈጻጸማቸው ሁሉ ይመራቸዋል።” ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አደረገው፤ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሙሴ እጆቹን በኢያሱ ራስ ላይ ጭኖ ከዚያ በኋላ የእርሱ ተተኪ መሆኑን በግልጥ አስታወቀ።
ዘኍል 27:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤ ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ። እናንተ በጺን ምድረ በዳ ማኅበሩ በተገዳደረኝ ጊዜ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው። ሙሴም ጌታን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የሥጋ ለባሽ ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆነ ጌታ በማኅበሩ ላይ አንድ ሰው ይሹም። እርሱም የጌታ ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በእነርሱ ፊት የሚወጣ በእነርሱም ፊት የሚገባ እየመራቸውም የሚያስወጣቸው የሚያስገባቸው ሰው ይሁን። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በእርሱ ላይ ጫንበት፤ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት። በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በጌታ ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበሩም ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ።” ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ ጌታም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በእርሱ ላይ ጫነበት፥ አዘዘውም።