የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 27

27
የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች
1የሰለጰዓድም ሴቶች ልጆች ቀረቡ፤ እርሱም ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገኖች፥ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጅ የኦፌር ልጅ ነበር፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። 2በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር በአለቆቹም በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፦ 3“አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኃጢአት ሞተ እንጂ ቆሬን በመከተል በጌታ ላይ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም። 4ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን።” 5ሙሴም ነገራቸውን በጌታ ፊት አቀረበ።
6ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 7#ዘኍ. 36፥2።“የሰለጰዓድ ልጆች ትክክለኛ ነገር ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ወደ እነርሱ ይተላለፍ። 8ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ‘ወንድ ልጅ ሳይኖረው የሚሞት ሰው ቢኖር፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይተላለፍ፤ 9ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ትሰጣላችሁ፤ 10ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ትሰጣላችሁ፤ 11አባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ትሰጣላችሁ እርሱም ይውረሰው፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዓትና ፍርድ ይሁን።’ ”
ሙሴ በፋንታው ኢያሱን መሾሙ
12 # ዘዳ. 3፥23-27፤ 32፥48-52። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤ 13ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ። 14እናንተ በጺን ምድረ በዳ ማኅበሩ በተገዳደረኝ ጊዜ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው።
15ሙሴም ጌታን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 16የሥጋ ለባሽ ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆነ ጌታ በማኅበሩ ላይ አንድ ሰው ይሹም። 17#1ነገ. 22፥17፤ ሕዝ. 34፥5፤ ማቴ. 9፥36፤ ማር. 6፥34።እርሱም የጌታ ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በእነርሱ ፊት የሚወጣ በእነርሱም ፊት የሚገባ እየመራቸውም የሚያስወጣቸው የሚያስገባቸው ሰው ይሁን። 18#ዘፀ. 24፥13።ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በእርሱ ላይ ጫንበት፤ 19በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው። 20የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት። 21#ዘፀ. 28፥30፤ 1ሳሙ. 14፥41፤ 28፥6።በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በጌታ ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበሩም ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ።” 22ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ 23#ዘዳ. 31፥23።ጌታም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በእርሱ ላይ ጫነበት፥ አዘዘውም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ